የኢማን አዕማድ

0
205

የኢስላማዊ እምነቶች አዕማድ ቁርዓንና ሐዲስ ባስረዱት መሰረት ስድስት ሲሆኑ እነሱም በአላህ ፣ በመልአኮች፣በመፃህፎቹ፣ በመልዕክተኞች በመጨረሻው ቀንና በአላህ ውሳኔዎች (ቀደር) ማመን ናቸው፡፡  አላህ እንዲህ ይላል፡-

لَيْسَ الْبِرَّ أَنْ تُوَلُّوا وُجُوهَكُمْ قِبَلَ الْمَشْرِقِ وَالْمَغْرِبِ وَلَكِنَّ الْبِرَّ مَنْ آمَنَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ وَالْمَلَائِكَةِ وَالْكِتَابِ وَالنَّبِيِّينَ
“መልካም ስራ ፊቶቻችሁን ወደ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም ፤ ግን መልካም ስራ በአላህና በመጨረሻው ቀን በመላእክትም በመፃህፍትም በነበቢያትም ያመነ ሰው …” (አል በቀራህ 177)
إِنَّا كُلَّ شَيْءٍ خَلَقْنَاهُ بِقَدَرٍ
“እኛ ሁሉን ነገር በልክ (በቀደር) ፈጠርነው” (አል ቀመር 49)
يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا آمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي نَزَّلَ عَلَى رَسُولِهِ وَالْكِتَابِ الَّذِي أَنْزَلَ مِنْ قَبْلُ وَمَنْ يَكْفُرْ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا بَعِيدًا
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መፅሀፍ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መፅሀፍ እመኑ ፤ በአላህና በመላእክቱም በመፃህፍቱም በመልክተኞቹም በመጨረሻውም ቀን የካደ ሰው (ከውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ” (አን ኒሳእ 136)

ነብዩም ስለ ኢማን ተጠይቀው እንዲህ በማለት መልሰዋል

“ኢማን በአላህ በመልአኮቹ፣ በመፅሐፎቹ ፣ በመልክተኞቹ በመጨረሻው ቀንና ጥሩም ይሁን መጥፎ በአላህ ውሳኔ (ቀደር) ማመን ነው”

እነዚህ ስድስቱ የኢማን መሰረቶች የትክክለኛ አማኞች (የአህሉ ሱና) እምነቶች ናቸው፡፡ሶሀቦች በታላቁ አስተማሪና መሪ አማካኝነት የመጣላቸውን ቁርአናዊ ትምህርት አምነውና ተቀብለው ከመፈፀማቸውም በላይ የነብዩን አስተምህሮት በታላቅ እንክብካቤና ጥረት ለሚቀጥለው ትውልድ (ታቢዒዮች) አስተላለፉ፡፡ ታቢዒዮችም በተመሳሳይ መልኩ እያስተላለፉ በተዋረድ ወደኛ ደረሰ፡፡ በዚሁ መልክ ዕለተ ቂያማ እስኪቃረብ ድረስ ትክክለኛው እምነት እንደተጠበቀ ይቀጥላል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ
“እኛ ቁርአንን እኛው አወረድነው ፤ እኛው ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን” (አል ሒጅር 9)

 ነቢዩም እንዲህ ብለዋል፦

“ከህዝቦቼ የተወሰኑ ቡድኖች እስከ እለተ ቂያማ ሀቅን በመያዝ የበላይ ከመሆን አይወገዱም፤ እነርሱን ያዋረደ አይጎዳቸውም”

ይሁንና ከትክክለኛው ምንጭ (ከቁርአንና ሐዲስ) ያልተቀዳውን የተሳሳተ እምነት በመያዝ ከነብዩና ከሶሀቦች መንገድ የሚያፈነግጡ ቡድኖችም እንደሚፈጠሩም ነብዩ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦

“የኔ ህዝቦች በሰባ ሦስት ቡድኖች ይከፋፈላሉ አንዱ ሲቀር ሁሉም እሳት ገቢ ነው:: እሱም እኔና ሰሀቦቼ ባለንበት ላይ የተገኘ ነው”

ማንኛውም ሰው ትክክለኛውን እምነት በመሳት ወደ ጥመት መንገድ ሊጓዝ የሚችለው የነብዩን አስተምህሮትን (ሱናን) ወደኋላ ትቶ በፍልስፍናና የኢስላም ጠላቶች በሚያመጡት የጥመት መንገድ ላይ ሲዘፈቅና በቁርዓንና ሐዲስ ላይ የሚኖረው ዕውቀትና እምነት በደከመ ቁጥር ነው፡፡  አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَمَنْ أَعْرَضَ عَنْ ذِكْرِي فَإِنَّ لَهُ مَعِيشَةً ضَنْكًا وَنَحْشُرُهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ أَعْمَى فَمَنِ اتَّبَعَ هُدَايَ فَلَا يَضِلُّ وَلَا يَشْقَى

“መሪየን የተከተለ አይሳሳትም አይቸገርምም :: ከግሳፄዬም የዞረ ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው ፤ በትንሳኤም ቀን እውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን” (ጣሃ 123−124)

ነብዩ ከትክክለኛው መንገድ የሚያፈነግጡ ቡድኖች እንደሚመጡና የጥፋታቸውም መንስኤ የሳቸውን መንገድ (ሱንና) መተው መሆኑን ሲናገሩ ለዚህ ችግር መፍትሔው ወደ ሱናቸው መመለስ እንደሆነም አክለው ገልፀዋል፡፡      ነብዩ እንዲህ ይላሉ፦

“ከናንተ ውስጥ ወደፊት የሚኖር ብዙ ልዩነቶችን ያያል ይህን ጊዜ የኔንና የቅን ምትኮቼን መንገድ አደራችሁን በመንጋጋ ጥርሳችሁ ነክሳችሁ ያዙት አዲስ ፈጠራዎችን ተጠንቀቁ ፈጠራዎች መመሪያ የሌላቸው (ቢድዓ) ናቸው፡፡ ቢድዓዎች ሁሉ ደግሞ ጥመት ናቸው፡፡ ጥመቶች ደግሞ የእሳት ናቸው”

ይሁንና ሸይጣንና ጓዶቹ የኢስላም ጠላቶች ኢማንን በማጠልሸትና ክህደትን በማሸብረቅ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ከቁርዓናዊና ሐዲሳዊ እምነት ለማስወጣት ከመጣር የሚተኙ አይደሉም::                                   ኢብኑ መስዑድ እንዲህ ይላሉ፡-

“ነብዩ ቀጥተኛ መስመር በማስመር ከመስመሩ በስተቀኝና በስተግራ ጭረቶችን አድርገው “እነዚህ መንገዶች እያንዳዱ ላይ ሸይጣን በመቆም ይጣራል” ካሉ በኋላ ይህንን ቁርዓን አነበቡ፡-

وَأَنَّ هَذَا صِرَاطِي مُسْتَقِيمًا فَاتَّبِعُوهُ وَلَا تَتَّبِعُوا السُّبُلَ فَتَفَرَّقَ بِكُمْ عَنْ سَبِيلِهِ
“ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው ፤ ተከተሉት ፤ (የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፤ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋቹኋልና” (አል አንዓም 153)

በኢስላም ታሪክ ውስጥ ከመጀመሪያው አጥፊ አይሑድ አብደላህ ኢብን ሰበእ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ኢማንን ለማጉደፍ የሚሞክሩና አማኞችን በተለያዩ ፍልስፍናዎች በመዝፈቅ ከኢማን የሚያስወጡ የሰው ሸይጣኖች ብቅ ቢሉም አላህ ደግሞ ይህን እምነት እንደሚጠብቅ ቃል ስለገባ ለአሳሳቾች ልጓም በማጉረስ ፅድት ያለውን ቁርዓናዊና ሀዲሳዊን እምነት ለሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚገልፁ ዑለማዎችን ይፈጥራል፡፡

እነዚህ የአላህ ወታደሮች ለኢስላም ጠላት የእግር እሳት በመሆናቸው ከተቻላቸው በመግደልና በማሰቃየት ወይም ደግሞ “ካፊር ነው” “የአባቶቻችንን መንገድ የሚቃረን ነው” እና በመሳሰሉ የስም ማጥፋት ድርጊቶች ሙስሊሙን ህብረተሰብ በማምታታት ልክ የመካ ከሀዲያን ነብዩን መተተኛ ገጣሚና የአባቶቻቸውን መንገድ አበላሽ እንደሆኑ አድርገው ተከታይ እንዳይኖራቸው የሚያደረጉትን አይነት ጥረት ያደርጋሉ፡፡

ነገር ግን የሰው ልጅ ከእንስሳዎች የተለየበት አእምሮ ባለቤት በመሆኑ ሀቅን በሀቅነቱ ሀሰትን በሀሰትነቱ ለመረዳት ከዓለማቱ ጌታ ለፍጡራኖቹ ከማንም ይበልጥ አዛኝና የሚበጃቸውን አዋቂ ከሆነው አላህ የመጣላቸውን ቁርዓንና ከስሜታቸው በመነሳት ሳይሆን ከአላህ የሚመጣላቸውን ራዕይ ብቻ አስተላላፊ ከሆኑት ነቢያችን የተላለፈላቸውን ሐዲስ ሊያጤን ይገባዋል፡፡ ልዩ ክብር ያጎናፀፈውን አእምሮ በመጠቀም ከአእምሮ ፈጣሪ የመጣለትን አስተምህሮት የማይከተል ከሆነ ግን በሚከተለው አንቀፅ አላህ ከእንስሳዎች ከመሰላቸው ሠዎች ይመደባል፡፡

 وَلَقَدْ ذَرَأْنَا لِجَهَنَّمَ كَثِيرًا مِنَ الْجِنِّ وَالْإِنْسِ لَهُمْ قُلُوبٌ لَا يَفْقَهُونَ بِهَا وَلَهُمْ أَعْيُنٌ لَا يُبْصِرُونَ بِهَا وَلَهُمْ آذَانٌ لَا يَسْمَعُونَ بِهَا أٌولَئِكَ كَالْأَنْعَامِ بَلْ هُمْ أَضَلُّ ۚ أٌولَئِكَ هُمُ الْغَافِلُونَ
“ከጋኔንም ከሰዎችም ብዙዎችን ለጀሐነም በእርግጥ ፈጠርን ፤ ለነርሱ የማያውቁባቸው ልቦች ፣ የማያዩባቸው አይኖች፣ የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሏቸው፤ እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው፤ እንዲያውም እነርሱ የባሰ የጠመሙ ናቸው፤ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው” (አል አዕራፍ 179)

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅ በጥመት መንገድ እንዲጓዝ አይፈቅድም፡፡ የሰው ልጅ ግን ዘውትር በእምቢተኛነቱ በመፅናት በግልፅ የአላህን መልዕክትና ትዕዛዝ ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡ የተላኩለትን መልዕክተኞችም ከመስማት ቸል ብሏል፡፡ በመልዕክተኞቹም አፊዟል አንገሏቷቸዋል አሳድዷቸዋል፡፡

እጅግ አዛኝና እጅግ ርህሩህ በመሆኑም በየዘመናቱ ለመልዕክተኞቹ መፃህፍት እየሰጠ የሰው ልጅ ከጥመት ጐዳና እንዲወጣና ሲፈጠር ጀምሮ የተዘጋጀለተን ኢስላማዊ የአቂዳ እምነት እንዲከተል ቸርነት ሲያደርግለት ቆይቋል፡፡

የሰው ልጅ ግን በግልፅ ከሚፈፅመው በተጨማሪ እውነተኛውን የኢስላማዊ የአቂዳ እምነት መንገድ የተከተለ ማስመሰል በስውር ጥመትና ሽርክ፣ ስውር ባሀድ አምልኮና ጣዖት ተተብትቦ ይገኛል፡፡

إِنَّ الدِّينَ عِنْدَ اللَّهِ الْإِسْلَامُ
‹‹አላህ ዘንድ (ተቀባይነት ያለው) ሃይማኖት ኢስላመ ብቻ ነው›› (አል ዒምራን 19)

በዚህ የቁርአን አንቀጽ እውነተኛ የኢስላማዊ አቂዳ ተከታይ ይረጋጋል፡፡

 شَرَعَ لَكُمْ مِنَ الدِّينِ مَا وَصَّى بِهِ نُوحًا وَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَى وَعِيسَى أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوا فِيهِ
‹‹ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፡፡ ያንንም ወዳንተ ያወረድነውን ያንንም በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ ማለትን (ደነገግን)፡፡›› (አል ሹራ 13)

ነብያችንም (ሰ.ዐ.ወ) ይህን አስመልክቶ በርካታ ሐዲሶችን ተነግረዋል፡፡ ሲመክርን፡-

‹‹የእኔን ሱና ያዙ፣ ከእኔ በኃላም የቅን ኸሊፋዎች (አል ኹለፋሁራሺዲን) ሱናም ያዙ፣ ተመሩበትም፣ በጥርሳችሁ ነክሳችሁ በደንብ ያዙት፤ አዳዲስ ፈጠራቻችን ተጠንቀቁ፡፡ አዳዲስ ለፈጠራዎች ሁሉ ቢድዓ ናቸው ቢድዓ ሁሉ ጥመት ነውና፡፡›› አቡዳውድ እንደዘገቡት