እውን ሙዚቃና ዘፈን በኢስላም አልተከለከለምን???

0
150

እውን ሙዚቃና ዘፈን በኢስላም አልተከለከለምን???

@ ሙሀመድ ሀሰን ማሜ

አንደሚታወቀው ኢስላም ሰፊና ጥልቅ አስተምህሮቶች፤ ረቂቅና ጥልቅ መመሪያዎችና ድንጋጌዎች አሉት፡፡ ሁሉንም የህይወት ዘርፎች  ዳሷል።  ሳያስተምረን ያለፈው የህይወት ጉዳይ የለም። በተለያየ መልክና ዘዴ እያንዳንዱን የህይወት ክፍል በመዳሰስም ወደር የሌለው ሃይማኖት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህንንም እውነታ የማንኛውም አማኝ ልቦናና ህሊና ያውቀዋል፡፡

ሆኖም በኢስላም ድንጋጌ እና መመሪያ ላይ በየጊዜው እና በየወቅቱ የተለያዩ ብዥታዎችና ውዥንብሮችን የሚፈጥሩ ሰዎች አልጠፉም፣ ነበሩም፣ አሉም፣ ይኖራሉም፡፡ በየጊዜው ብቅ ጥልቅ ከሚሉ በርካታ ውዥንብሮች መካከል የሙዚቃን ብይን የተመለከተው ይጠቀሳል። የራሳቸውን ግንዛቤ ለማስተላለፍ ሲፈልጉ፤ ኢስላም ስለዘፈንም ይሁን ስለሙዚቃ ክልክልነት የተናገረው ነገር የለም፡፡ ክልክል ለመሆኑ የቀረቡ መረጃዎችንም የወደቁና ተቀባይነት የሌላቸው እንደሆኑ፤ ሲጠኑ በሁለት እግር መቆም የማይችሉ  እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ የሚነዙት ብዥታ ተራ አሉባልታ እንደሆነ በእዚህ መልዕክቴ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ በተለይም ሰሞኑን አቶ ሀሰን ታጁ በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ የጣዕም ልኬት የሙዚቃ ዝግጅት ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ይህ አይነቱን አመለካከት በስፋት ስላብራራ አጠር ያለ ምላሽ አዘጋጅቻለው። አላህ ስራችንን ሁሉ በኢኽላስ የተፈፀመ እንዲያደርገውነ እለምነዋለሁ።  እግዛንም ከእርሱ ብቻ እጠይቃለሁ፡፡

       ዘፈንና ሙዚቃ በኢስላም የተከለከለ መሆኑን በተለያዩ ኢስላማዊ መረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

1ኛ- ከቁርአን                  2ኛ- ከሐዲስ

3ኛ- ከሰሃቦች                  4ኛ- ከታቢዒዮች

5ኛ- ከአራቱ መዝሃቦች     6ኛ – ከኢጅማዑ አሰለፍ

1ኛ- ከቁርአን

በሱረቱል ሉቅማን ቁጥር 6

وَمِنَ النَّاسِ مَن يَشْتَرِي لَهْوَ الْحَدِيثِ لِيُضِلَّ عَن سَبِيلِ اللَّهِ بِغَيْرِ عِلْمٍ وَيَتَّخِذَهَا هُزُوًا ۚ أُولَٰئِكَ لَهُمْ عَذَابٌ مُّهِينٌ [٣١:٦]

“ከሰዎች ያለ እውቀት ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስትና ማላገጫ አድርጎ ሊይዛት አታላይ ወሬን (ለህወል ሀዲስ) የሚገዛ አለ፤ እነዚያ እነሱ አዋራጅ ቅጣት አላቸው፡፡”

በእዚህ አንቀፅ ውስጥ “ለህወል ሀዲስ” (አታላይ ወሬ) ተብሎ የተሰየመውና ቅጣቱም አወራጅ ተብሎ የተዛተበት ምን ይሆን? መልሱን ከሰሃቦች ማግኘት ይቻላል፡፡

ሀ. አብድላህ አብኑ መስዑድ

(ስለቁርአን ጥልቅ እውቀት ባላቸው ስመጥር ሰሃባ አንዱ ነው፡፡) ስለ “ለህወል ሀዲስ” (አታላይ ወሬ) ሲጠየቅ ሶስት ጊዜ በመማል “ዘፈን ነው ዘፈን ነው ዘፈን ነው” በማለት መመለሱን ኢብኑ አቡ ሸይባ፣ ኢብኑ ጀሪር፣ አልሃኪም፣ አልበይሀቂ እና ኢብልጀውዚ ዘግበውታል፡፡

ለ. አብደላህ ኢብኑ ዐባስ

(የዑማው አዋቂና በቁርአን ማብራሪያ ላቅ ያለ እውቀት ያለውና ረሱልም “አላህ ሆይ ሃይማኖቱን አስገንዝበው የቁርአንንም ማብራሪያ አሳውቀው፡፡” ብለው ዱዓእ ያደረጉለት ስመ ጥር ሰሃባ ነው፡፡) ስለ (ለህወል ሀዲስ) “ዘፈንና መሰሎቹ ናቸው” ማለቱን ኢብኑ አቡ ሸይባ፣ ቡኻሪ፣ ኢብኑ ጀሪር፣ አልበይሀቂ፣ እና ኢብኑ ጀውዚ ዘግበውታል፡፡

ሐ. አብደላህ ኢብኑ ዑመር (የመዲና ሙፍቲና የፊቂህ ምሁር ) ለህወል ሀዲስን በማስመልከት “እርሱም ዘፈን ነው” በማለት አብራርቶታል፡፡

መ. ጃቢር ኢብኑ አብደላህ  (ከኢብኑ ዑመር ቀጥሎ የመዲና ሰዎች ፊቂህ እንዲሁም ሙፍቲ የነበረው) “ዘፈንና ማድመጡ ነው” ማለቱን ኢብኑ ጀሪር ዘግበዋል፡፡

ታዲያ ከእነዚህ ታላላቅና ስመጥር ሰሃቦች ይህን አንቀፅ በተመለከተ (ዘፈን) መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የሰሃቦች ማብራሪያ ማስረጃ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህንም ማብራሪያ የተቃረነ አንድም ሰሃባ የለም፡፡

ሰሃቦችም እንዲህ ብለው እንደተረጐሙት ሁሉ ታቢዒዮችም በተመሳሳይ መልኩ አብራርተውታል፡፡ እንደሚከተለውም ዝርዝራቸውን እጠቅሳለሁ፡፡

1.ሙጃሂድ ኢብኑ ጃቢር     2. ዒክሪማህ         3. መክሁል   4.ኢብራሂም አል ነኸዒ     5. ዐጣእ

6.ሰዒድ ኢብኑ ጁበይ   7.አል ሐሰን አል በስሪ     8. ቀታዳህ ኢብኑ ደዓማ

9. መይሙን ኢብኑ ሚህራን       1ዐ. ሀቢብ ኢብኑ አቢሳቢት       11. ዐምር ኢብኑ ሹዓይብ  

12.  አብዱልመሊክ ኢብኑ ጁረይጅ     13. ሰኢድ ኢብኑልሙሰይብ ናቸዉ፡፡

ሱረቱ ነጅም ቁጥር 59 – 61

أَفَمِنْ هَٰذَا الْحَدِيثِ تَعْجَبُونَ [٥٣:٥٩]وَتَضْحَكُونَ وَلَا تَبْكُونَ [٥٣:٦٠]وَأَنتُمْ سَامِدُونَ [٥٣:٦١]

“በዚህ ንግግር ትደነቃላችሁን?! ትስቃላችሁምን? አታለቅሱምን? እናንተም ዘንጊዎች ናችሁ፡፡”

ይህንም አንቀፅ በማስመልከት ዘንጊዎች ተብሎ የተተረጐመው ቃል በአረብኛው “ሳሚዱን” የሚለው ቃል ሲሆን ትርጉሙን በተመለከተ የየመን ቋንቋ እንደሆ በመጥቀስ “ዘፈን” እንደሆነ አብደላህ ኢብኑ ዐባስ ፣ ሙጃሂድ፣ ዒክሪማና አደሃክ ተናግረዋል፡፡

ሱረቱል ኢስራእ ቁጥር 64

وَاسْتَفْزِزْ مَنِ اسْتَطَعْتَ مِنْهُم بِصَوْتِكَ وَأَجْلِبْ عَلَيْهِم بِخَيْلِكَ وَرَجِلِكَ وَشَارِكْهُمْ فِي الْأَمْوَالِ وَالْأَوْلَادِ

“ከእነሱ ያቻልከውንም ሰው በድምፅህ አታል በእነሱም ላይ በፈረሶኞችህም ለልብ በገንዘቦቻቸውም፣ በልጆቻቸውም ተጋራቸው፡፡”

ሙጃሂድ ኢብኑ ጃብር (የአብደላህ ኢብኑ ዓባስ ታላቅ ተማሪ) የኢብሊስ ድምፅ ምንነት ሲገልፁ እንዲህ ነበር ያሉት፡፡ “እርሱም ጊና (ዘፈን)፣ ሙዚቃ መሳሪያ፣ ላግጣና  ከንቱ ነገር ነው፡፡”

አድሃክም የዘፋኝ (የሙዚቃ መሳሪያ) ድምፅ ነው” ብለዋል

ኢብኑል ቀይምም እንዲህ በማለት ስለዘፈን ሁኔታ ይገልፃሉ :-

“ዘፈን ከታላላቅ የሰይጣን ድምፃችና ነፍስን የሚያስበረግግበት፣ የሚረብሽበት እና ሰላም የሚነሰት ለመሆኑ አያጠራጥርም የቁርአን ወደሚረጋጋበት፣ ሰላም የሚያገኝበትና ወደጌታዋ እንድትመለስ የሚያደርገውን ተቃራኒ ነው፡፡”

ሱረቱል ሀጅ ቁጥር 3ዐ

وَاجْتَنِبُوا قَوْلَ الزُّورِ [٢٢:٣٠]

“ሐሰትንም ቃል ራቁ”

መሐመድ ኢብኑል ነፍያ “የሐሰት ቃል” ተብሎ የተተረጐመውን “ቀውለ ዝዙር” ሲያብራሩ “እርሱ ዘፈን ነው” በማለት ገልፀዋል፡፡

ሱረቱል አንፋል ቁጥር 35

وَمَا كَانَ صَلَاتُهُمْ عِندَ الْبَيْتِ إِلَّا مُكَاءً وَتَصْدِيَةً  [٨:٣٥]

“በቤቱ ዘንድም (በከዕባ) ስግደታቸው ማፏጨትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡”

“ማፏጨትና ማጨብጨብ” የሚለውን ትርጉም የተወሰደው (ሙካአን ወተስዲየተን) ከሚለው ቃል ሲሆን መልዕክቱን በተመለከተ ዘፈንን ለማለት እንደተፈለገ በርካታ የቁርአን ሙፈሲሮች ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህም ግንባር ቀደም ሙፈሲሮች አብደላህ ኢብኑ ዓባስ፣ አብደላህ ኢብኑ ዑመር፣ ኢብኑ ጁበይር ፣ ቀታዳ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

የዘፈንን ፍርድ የሚገልፁና የሚያብራሩ የቁርአን አንቀፆችና ማብራሪያቸውን እንደተመለከትነው ዘፈንና ሙዚያቃን አበክረው እንዳወገዙና እንደተቹ እንመለለከታለን፡፡

በመቀጠልም ወደ ሁለተኛው መረጃችን ሐዲስ እንመጣለን፡፡

2ኛ. ከሀዲስ

2.1 ኢማሙ ቡኻሪ አቡ ማሊክ አል አሸዓሪን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት ረሱል

“ከእኔ ዑመት ውስጥ፣ ዝሙትን፣ ሐርን አስካሪ መጠጥን እና ሙዚቃን ልክ እንደሐላል የሚይዙ ይመጣሉ” ብለዋል ይህ ሐዲስ ሙዚቃንና መሰሎቹን ሐራም እንደሆነ ያመለክታል ይሄውም “አንደ ሐላል” የሚለው ቃል ተከልክሎ እያለ ግና እነሱ እንደሐላል አድርገው መጠቀምንንና መያዛቸው ተችተው አግለፃቸው ነው፡፡

2.2 አብዱራህማን ኢብኑ ዓውፍ እንዳስተላለፉት መልዕክተኛው                 

“እኔ የተከለከልኩት ከሁለት ጠማማና ቂል ከሆኑ ድምፆች ነው”

ሀ. የደስታ ጊዜ ጩኸት ይሄውም ለህው (ላግጣ) (ጩኸቶች) ለዒብ (ጫወታ) እና የሰይጣን መሰንቆ፣

ለ. የአደጋ ጊዜ ጩኸት (ድምፅ) ማለትም “ፊትን መቧጠጥ፣ ልብስን መተርተርና የሰይጣን ድምፅ ናቸው”

(ቲርሚዚ፣ ሐኪም፣ ኢብኑ ሰዕድና ሌሎችም ዘግበውታል)

በዚህ ሐዲስ ላይ ረሱል ﷺ የሙዚቃ መሳሪያ “የሰይጣን” ብለው መግለፃቸው ከዚያም በፊት “የተከለከልኩት” ማለታቸው ዘፈን የተከለከለ እንዲሁም የሰይጣን ተግባር መሆኑን በግልፅ የሚያስረዳን መረጃ ነው፡፡

2.3 ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ ይህን ሐዲስ በማስመልከት እንዲህ ብለዋል :-

“ይህ ሐዲስ ዘፈን ሐራም ነው ተብሎ ለማስረጃነት ከሚቀርቡት ሁላ በጣም ምርጡ ነው፡፡”

2.4 ኢማሙ ቲርሚዙ ዒምራን ኢብኑ ሁሰይንን ዋቢ በማድረግ ከነብዩ ﷺ እንዳስተላለፉት

“በዚህ ህትብ ላይ ምድር ተከፍታ መስመጥ፣ የመልክ መቀየርና በድንጋይ መቀጥቀጥ ይከሰታል” ሲሉ ከሙስሊሞች አንዱ “መቼ ነው?” ብሎ ሲጠይቅ መልዕክተኛውም “ዘፋኝ ሴቶችና ሙዚቃ ይፋ ሲወጡ እንዲሁም አስካሪ መጠጥ በግልፅ የተጠጣ ጊዜ ነው፡፡” በማለት መለሱለት

2.5 ኢማሙ ሙስሊም አቡሁረይራን ዋቢ በማድረግ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ማለታቸው ዘግበዋል “ደውል የሰይጣን መሰንቆ ነው፡፡”

2.6 አቡ ዑበይድ፣ ኸላል፣ በይሃቂና በገዊ አቡሁረይራን ዋቢ በማድረግ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ “በዘፈን የሚገኝን ገቢ ከልክለዋል፡፡”

እነዚህንና መሰል ሀዲሶችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ግና አስተዋይ እና አህምሮ ያለው በርካታ ሳይሆን አንድና ግልፅ መረጃ ከመጣለት ይበቃዋል፡፡ ቢሆንም ነገሩ አላህ “የጠፋ ሰው ከአስረጅ በኃላ (መረጃ ከመጣለት በኃላ) እንዲጠፋ፣ ሕያው የሚሆን ሰው ከአስረጅ በኃላ ሕያው እንዲሁን” እንዳለው ስለሆነ ነው፡፡

3ኛ. ከሰሃቦች

ልክ ቁርአንና ሐዲስ የሰጣቸውን መልዕክት የሚያረጋግጥ ንግግርና አቋም ነበራቸው በዘፈን ላይ ከቁርአንና ከሐዲስ መመሪያ ሊወጡ ስለማይፈልጉ ለማንውም የእነርሱንም አቋም መመልከቱ ያስፈልጋል፡፡

3.1 አቡበክር አሲዲቅ ሁለት ትናንሽ ሴት ልጆች ድቤ እየመቱ ሲዘፍኑ አዩዋቸውና ከለከሏቸው እንዲህ አሉ

“የሸይጣን ዝማሬ (ማሲንቆ) ነው፡፡” ነብያችንም አይተዋቸው አልተቃወሟቸውም፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

3.2 ዑስማን ኢብኑ ዓፋን ከዚህ ቀደም በዚህ ወንጀል ላይ እንዳልወደቁ የአላህን ፀጋ ሲያወሳ እንዲህ በማለት ነበር፡፡ 

“አልዘፈንኩም አልተመኘሁምም”  (ኢብኑ ዓሲምና ጠበሪ ዘግበውታል)

3.3 አብደላህ ኢብኑ መስዑድ

“ማንኛውም ግለሰብ ሲጋልብ የአላህን ስም ካላወሳ ሰይጣን አብሮት ይፈናጠጣል እንዲህም ይለዋል “ዝፈን” የማይችል ከሆነ ደግሞ “ተመኝ” ይለዋል፡፡ ማለቱን (አብዱረዛቅ፣ ጠበራኒና ኢብኑ አቢ አዱንያ ዘግበውታል፡፡)

3.4 በድጋሚም እንዲህ ብሏል

“ዘፈን ልብ ውስጥ ኒፋቅን (አስመሳይነትን) ያበቅላል ውሃ አዝእርትን (አትክልትን) እንደሚያበቅል ሁሉ ዚክር (አላህን ማውሳት) ደግሞ ኢማንን በልብ ውስጥ ያበቅላል ልክ ውሃ በቆልትን እንደሚያበቅል” (ኢብኑ አቢ ዱንያና በይሀቂ ዘግበውታል፡፡)

3.5 እንዲህም ብሏል “ዘፈን የዝሙት ማጪያ ነው፡፡”

3.6 አነስም እንዲህ ብሏል

“ (ከገቢው ምንጭ) ሁሉ መጥፎው የዘፋኝ የገቢ ምንጭ ነው፡፡”

3.7 አብደላህ ኢብኑ ዑመር ሐጅ ወይም ዑምራ ለማድረግ የነየቱ (ያሰቡ) ሰዎች አጠገብ ሲያልፍ ከመሃላቸው የሚዘፍን ሰው ሰማ እንዲህም በማለት ዱዓእ አደረገባቸው “አላህ ጥሪያችሁን አይቀበል እረ! ጥሪያችሁን አይቀበል፡፡”

3.8 አሁንም በድጋሚ አንዲት ህፃን ልጅ ስትዘፍን አየና እንዲህ አለ

“ሰይጣን ማንንም ቢተው (ቢያልፍ) ኖሮ ይህችን ልጅ ይተው (ያልፍ) ነበር፡፡”

3.9 እናታችን አኢሻ አንድን ሰውዬ እየዘፈነና ጭንቅላቱን እየወዘወዘ ቤት ውስጥ አየችውና

“ኡፍ ሰይጣን አስወጡት አስወጡት” አለች ከዚያም ከቤት አስወጡት

3.1ዐ አብደላህ ኢብኑ ዓባስ

“ከበሮ ሐራም ነው፣ ሙዚቃም ሐራም ነው …”

4ኛ. ከታቢዒዮች

ታቢዒዮችም በበኩላቸው ሐራምነቱን ካለምንም ልዩነትና ውዝግብ ተስማምተውበታል ንግግራቸውና አቋማቸውንም እንደሚከተለው እንገልፃለን፡፡

4.1 ወኪዕ ኢብኑል ጀራህ እንዲህ ብለዋል

“ኢብኑ ዑመር እንዳደረጉት ጥሩንባውን (ዋሽንቱን) ቀማውና ጭንቅላቱ ላይ ሰበረው”

4.2 ዘይኑል ዓቢዲን

“በርበጥ” (የሙዚቃ መሳሪያ ነው) ያለበት ማህበረሰብ ምን አልተባረከም” ይሉ ነበር፡፡

4.3 ራፊዕ ኢብኑ ሐፍስ አል መደኒ

“አራት አይነት ሰዎችን አላህ የትንሳኤ ትለት በእዝነት አይን አይመለከታቸውም ደጋሚ፣ አስለቃሽ፣ ዘፋኝ እና ባሏን ያታለለች” ማለታቸውን ኢብኑ አቢ አዱንያ ዘግበዋል፡፡

4.4 አንድ ሰውዬ አል ቃሲም ኢብኑ መሐመድን ስለዘፈን እንዲህ በማለት ጠየቃቸው

“ሐራም ነውን?” ለጠያቂውም “አላህ እውነትን ከውሸት ሲለይ ከየትኛው የሚያደርገው ይመስልሃል?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ሲመልስ እርሱም “ከውሸት ጋር” ሲላቸው እሳቸውም “እንደዚያው ነው” በማለት መልሱን ሰጡት” (አል በይሀቂ ዘግበውታል)

4.5 ሰዒድ ኢብኑል ሙሰይብም “በእርግጥም ዘፈንን እጠላለሁ” ማለታቸውን አብዱረዛቅ ዘግቧል

4.6 አሸዕቢ እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል

“ዘፋኝና የሚዘፈንለት ተረግመዋል፡፡”

4.7 አል ፉደይል ኢብኑ ዒያድ

“ዘፈን የዝሙት መወጣጫ (መሰላል) ነው፡፡” ብለዋል

4.8 መክሁል እንዲህ ብለዋል

“ዘፋኝ ቤቱ እያለች የሞት ሰው ላይ አንሰግድበትም፡፡”

4.9 ኢብራሂም ኢብኑል ሙንዚር እንዲህ ተጠየቁ

“ስለዘፈን (ዘፈንን) ታግራራላችሁ?” እንዲህ በማለት መልስ ሰጡ “በአላህ እንጠበቃለን! እኛ ዘንድ አመፀኞች እንጂ አያደርጉትም”

4.1ዐ ደሃክ

“ዘፈን ልብን የሚያበላሽ ጌታን የሚያስቆጣ ነው”

4.11 አል ሃሪስ አል ሙሃሲቢ

“ዘፈን እንደሙት (ሞት እንስሳ) ሐራም ነው፡፡”

 

5ኛ. የአራቱ መዝሃብ መሪዎች ስለ ዘፈን

5.1 ኢማሙ አቡ ሐኒፋ ዘፈንን አጥብቀው ከሚከለክሉት ነበሩ፣ ማድመጡንም እንደወንጀል ይቆጥሩት ነበር፡፡ የእሳቸው ባልደረቦችም (ተከታዮችም) የሙዚቃ መሳሪያን ማድመጥ ሐራም ነው ይሉ ነበር፡፡ በተጨማሪም ሙዚቃን ማድመጥ ወንጀል ነው ፣የሚዘፈንበት ቦታ መቀመጥ አመፅ ነው፣ በዘፈን መርካና መደሰት ክህደት ነው፡፡” እስከማለት ደርሰዋል

5.2 ኢማሙ ማሊክን የመዲና ሰዎች ዘንድ የተፈቀደ ዘፈን አለ እንዴ? ብለው ሲጠይቋቸው “እኛ ዘንድ ይህንን ተግባር የሚፈፅሙት አመፀኞች (ጋጠወጦች) ናቸው” በማለት ነበር መልስ የሰጡት

5.3 ኢማሙ ሻፊዒም ዘፋኝ ወንድና ሴት በማስመልከት “የአንዳቸውም የምስክርነት ቃል ተቀባይነት የለው ይህንም የፈፀመ ቂልና ክብረ ቢስ ይሆናል፡፡” ብለዋል “ይህም ግዴለሽነት ነው”

በተጨማሪም “ዒራቅ ውስጥ ተግቢር (ድቤ እየመቱ በዜማ ዚክር ማድረግ) የሚባል ነገር መናፍቃን ሰዎችን ከቁርአን ለመግታት የፈጠሩት አዲስ ነገር ጥዬ መጥቻለሁ፡፡”

5.4 ኢማሙ አህመድ “የሙዚቃ መሳሪያ ክራር፣ ከበሮ፣ ዋሽትና መሰሎቹ ሐራም ነው፡፡” አንድ ጊዜ አንድ ሰው ጀናዛ (አስክሬን) ለማጠብ ጠራኝና የከበሮ ድምፅ ሰማሁ” ብሎ ሲጠይቃቸው እሳቸውም “ከበሮውን መስበር ከቻልክ ስበረው ካልሆነ ግን ጥለህ ውጣ” በማለት መልስ ሰጡት::

6ኛ. ኢጅማዑ አሰለፍ

ኢጅማዕ ስንል በአንድነት ካለምንም ልዩነትና ውዝግብ በአንድ ድምፅ የፀደቀ ስምምነት ማለታችን ነው፡፡

በአንድ ድምፅ መስማማታቸውን የሚያመለክቱ ነገሮች

ሀ. እስካሁን እንደተመለከትነው ከሰሃቦችም ይሁን ከታቢዒዮች ይህን አቋም በትክክለኛ ዘገባ ተቃውሞ የመጣ አለመኖሩና ይህንም ጉዳይ የውዝግብ ጉዳይ አድርገው እንዳልወሰዱት የእጅቲሃድ (የግል ጥረት) የሚገባባት ጉዳይ እንዳልሆነ የጠነከረ ንግግራቸው ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ፡- አመፀኞ፣ የተረገመ፣ ሰይጣን፣ የሙዚቃ መሳሪያውን በሰዎቹ ጭንቅላት ላይ ሰብረው ገቢያቸው የከፋና የመሳሰሉትን ሀይለ- ቃል ባልተጠቀሙ ነበር፡፡

ለ. ከእነርሱም መሐል የፈቀደ መኖሩ ፍፁም አልተዘገበም

ሐ. የአራቱ መዝሃብ መሪዎችንም ንግግር እንዳስተዋልነው በጥንካሬ ማውገዛቸውን እንመለከታለን፡፡ ከወንጀል እንደቆጠሩት፣ የምስክርነት ቃሉ ውድቅ ከሚያደርበትና ክብሩን ከሚያጐድፍ ወንጀልና ተግባሪውንም ቅናት የሌለው ግዴለሽ ቂል ብለው የመደቡትና በግልፅ የሚያሳየው በአንድነት ያለምንም ተቃራኒ ሐራም መሆኑን ነው፡፡ የተወዛገቡበት ጉዳይ ቢሆን ኖሮ አስተያየታቸውን ሰጥተው ያልፋሉ እንጂ ይህን ያህል አያጠብቁም ነበር፡፡ እኛ ዘንድ እንዲህ ነው ስህተትም ሊሆን ይመቻል ይሉ ነበር ከፍትሃዊነታቸው የተነሳ፡፡ ምክንያቱም ይህን ያህል ካወሳን ሰለፎች (ቀደምቶቹ) ዘንድ በአንድ ድምፅ፣ በስምምነት ያለምንም ቅራኔ ሐራምነቱ የፀደቀ መሆኑን ከገለፁ ታላለቅና ስመጥር የኢስላም መሪዎች ጥቂቶችን እንጠቅሳለን፡፡

  1. አቡዑመር ኢብኑ አብዱልበር (ማሊኪይ)
  2. አቡዑመር ኢብኑ አስላህ (ሻፊዒይ)

3.አቡ አጠይብ አጠበሪ

4.አቡአብደላህ ኢብኑ በጣ አልዑክበሪ

5.ሸይኸል ኢስላም ኢብኑ ተይሚይ (ሀንበሊ)

  1. አቡበክር መሐመድ ኢብኑ አልሁሰይን አልአጁሪ

7.አቡልፈረጅ ኢብኑ ረጀብ

8.አቡያህያ አሳጂ

9.አቡዘከሪያ አነወዊ

10.አቡል ቃሲም አራፊዒ

11.ሙወፊቅ አዲን ኢብኑ ቀዳማ

12.ዒማዱዲን ኢብኑ ከሲር

13.አህመድ ኢብኑ ሀጀር አልሀይተሚ

14.ሳሊም ኢብኑ አዩብ አራዚ

15.ሸሃቡዲን አልአዝሩዒ

16.አቡበክር ኢብኑል ሙንዚር አነይሳቡሪ

17.ቡርሃኑ ዲን ኢብኑ አብዱልሐቅ (ሐነፊይ)

18.አቡል ወሊድ ኢብኑ ሩሽድ አልቁርጡቢ

19.ጀማሉዲን አልበርዚ

20.አብዱላህ ኢብኑ አቢ ዐስሮን

21.መሐመድ ኢብኑ አህመድ አልቁርጡቢ (ማሊኪ)

22.አቡጃዕፈር ኢብኑ ጀሪር አጠበሪ 23.ሸምሱዲን ኢብኑል ቀይም አልጀውዚያ

24.አቡኢስሃቅ አሸይራዚ

25.ሸምሱዲን አልጀውጀሪነ

26.ሸረፈዲን ኢብኑ ቁዳማ

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት 26 ታላላቅና ታዋቂ አሊሞች የዘፈንን ሐራምነት በአንድ ድምፅ ሁሉም የተስማማበት ጉዳይ መሆኑ በየኪታቦቻቸው እናገኛለን፡፡

ታላቁ ዓሊም ኢብኑ ሀጀር አልሀይተሚ ይህንን የጋራ ስምምነት በማስመልከት “ከዚህ ተቃራኒ የዘገበ በእርግጥ የተሳሳተ ወይም ስሜቱ እስኪያውረው ፣ እስኪያደነቁረውና ከቅኑ መመሪያ እስኪከለክለው ድረስ አሸንፎታል፡፡ ከሱናውና ከፈሪ- አላህነት (ከተቅዋ) አንሸራቶታል” ብለዋል።

እውን ሙዚቃና ዘፈን በኢስላም አልተከለከለምን