አላህን በጌትነቱ በብቸኛ ተመላኪነቱ በስሞቹ እና በባህሪያቱ ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ተውሂድ በ ሦስት የሚከፈል ሲሆን እነሱም፡
- ተውሂደ አል-ሩቡቢያህ:- አላህን በስራዎቹ አንድ ማድረግ፡፡ ይህም ማለት፤ መፍጠር፣ሲሳይን መስጠት፣ነገሮችን ማስተናበር፣ መግደል እና ህያው ማድረግ በመሳሰሉት ድርጊቶቹ አላህን ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ከአላህ ሌላ ፈጣሪ የለም፡፡ አላህ ይህንን እንዲህ በማለት ይገልፅልናል፡-
((اللَّهُ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ ۖ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ)) الزمر: ٦٢
(አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው) አል-ዙመር 62
ከአላህ ሌላ ሲሳይን የሚሰጥ የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-
((وَمَا مِن دَابَّةٍ فِي الْأَرْضِ إِلَّا عَلَى اللَّهِ رِزْقُهَا وَيَعْلَمُ مُسْتَقَرَّهَا وَمُسْتَوْدَعَهَا ۚ كُلٌّ فِي كِتَابٍ مُّبِينٍ )) هود: ٦
(በምድርም ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለም ሲሳዩ አላህ ዘንድ ያለ ቢሆን እንጂ) ሁድ 6
ከአላህ ሌላ ነገሮችን የሚያስተናብር የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-
((يُدَبِّرُ الْأَمْرَ مِنَ السَّمَاءِ إِلَى الْأَرْضِ )) السجدة: ٥
(ነገርን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያስተናብራል) አል-ሰጅዳህ 5
ከአላህ ሌላ ህያው ሊያደርግ እንዲሁም ሊገድል የሚችል የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-
((هُوَ يُحْيِي وَيُمِيتُ وَإِلَيْهِ تُرْجَعُونَ )) يونس: ٥٦
(እርሱ ህያው ያደርጋል ይገላልም ወደርሱም ትመለሳላችሁ) ዩኑስ 56
ይህን ዓይነቱን የተውሂድ ክፍል በረሱል ዘመን የነበሩ ከሀዲያን አጋሪዎች ያልካዱት ቢሆንም ከባዕድ አምልኮ ባለመላቀቃችዉ ወደ ኢስላም ሊያስገባቸው አልቻለም፡፡ አላህም ይህን የተውሂድ ክፍል ማረጋገጣቸውን በማስመልከት እንዲህ ይላል፡-
((وَلَئِن سَأَلْتَهُم مَّنْ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ لَيَقُولُنَّ اللَّهُ )) لقمان: ٢٥
(ሰማያትና ምድርንም የፈጠረ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይላሉ)ሉቅማን 25
2- ተውሂድ አል-ኡሉሂያህ
አላህን በአምልኮ አንድ ማድረግ፡፡ በዱዓእ (ልመና)፣ በፍራቻ፣በመመካት፣እርዳታን እና ጥበቃን በመጠየቅ እንዲሁም እርሱ ባሮቹን ባዘዘባቸው ሌሎች አምልኮቶች ሁሉ ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡ የአምልኮ ዓይነቶችን ሁሉ ያለምንም አጋር ለርሱ ብቻ ማድረግን ግዴታ ያደርጋል፡፡
ከአላህ ሌላ ማንንም አንለምንም፡፡ አላህ እርሱን ብቻ መለመን እንዳለብን ሲነግረን እንዲህ ይላል፡-
((وَقَالَ رَبُّكُمُ ادْعُونِي أَسْتَجِبْ لَكُمْ )) غافر: ٦٠
(ጌታችሁም አለ! ለምኑኝ እቀበላችኃለሁና) አል-ጋፊር 60
ከአላህ ሌላ አምልኮታዊ የሆነ ፍራቻን ማንንም ቢሆን አንፈራም፡፡ አላህ እንዲህ ይለናል፡-
((فَلَا تَخَافُوهُمْ وَخَافُونِ إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ )) عمران: ١٧٥
(አትፍሯቸውም አማኞች የሆናችሁ እንደሆነ {እኔን ብቻ} ፍሩኝ) አል-ኢምራን175
ከአላህ ሌላ በማንም አንመካም፡፡ አላህ አማኞች በእርሱ ላይ ብቻ ሊመኩ እንደሚገባ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-
((وَعَلَى اللَّهِ فَتَوَكَّلُوا إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ )) المائدة: ٢٣
(አማኞች እንደሆናችሁ በአላህ ላይ ብቻ ተመኩ) አል-ማዒዳህ 23
- ከአላህ ሌላ ፍጡራን በማይችሉት ጉዳይ ላይ እርዳታን ከአላህ ዉጪ ከማንም አንጠይቅም፡፡ ይህን በማስመልከት አላህ በሱረቱል ፋቲሀ ላይ ደጋግመን ምናነባቸዉን አንቀፆች አዉርዷል፡፡
((إِيَّاكَ نَعْبُدُ وَإِيَّاكَ نَسْتَعِينُ )) الفاتحة: ٥
(አንተን ብቻ እናመልካለን፤ ከአንተም ብቻ እርዳታ እንጠይቃለን) አል-ፋቲሀ 5
- ከአላህ ሌላ ከማንም ጥበቃን አንጠይቅም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
(( قُلْ أَعُوذُ بِرَبِّ النَّاسِ )) الناس: ١
የሰዎች ጌታ በሆነው እጠበቃለሁ በል) አል-ናስ 1
ይህ የተውሂድ ክፍል የአላህ መልዕክተኞች ለሰው ልጆች ለማስተላለፍ ከአላህ ይዘው የመጡት ዋነኛው መልዕክት ነው፡፡ ሁሉም ነብያቶቸ የዳዕዋቸዉ ዋና ተልዕኮ አምልኮን ባጠቃላይ ለአላህ ብቻ ማድረግ (ተውሂደል ኡሉሂያህ) ነው፡፡ ይህንን አላህ በቀጣዩ አንቀፅ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡፡
((وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ )) النحل: ٣٦
(በየህዝቡም ሁሉ ዉስጥ አላህን አምልኩ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልዕክተኞችን በእርግጥ ልከናል) አል ነህል 36
ይህንኑ የተውሂድ ክፍል እና የነብያቶች መልዕክት ነዉ የፊተኞቹ ሆኑ በዘመናችን የሚገኙ አጋሪዎች ያስተባበሉት፡፡ የመካ ሙሽሪኮች መልዕክተኛው አንድን አምላክ ብቻ አምልኩ ባሏቸው ጊዜ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ አላህ እንዲህ ይላል፡-
((أَجَعَلَ الْآلِهَةَ إِلَٰهًا وَاحِدًا ۖ إِنَّ هَٰذَا لَشَيْءٌ عُجَابٌ )) ص: ٥
(አማልክቶቹን አንድ አምላክ አደረጋቸዉን? ይህ አስደናቂ ነገር ነው‹አሉ›) ሷድ 5
አላህ በየዘመናቱ ከላካቸው ነብያት (ኑህ፣ሁድ፣ሳልህ እና ሹዓይብ) ጥሪ ይህን ይመስል እንደነበር በተለያዩ አንቀፆች ገልፆልናል፡-
((يَا قَوْمِ اعْبُدُوا اللَّهَ مَا لَكُم مِّنْ إِلَٰهٍ غَيْرُهُ ))
(ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ ከእርሱ በቀር ምንም አምላክ የላችሁም…) አል-አእራፍ 59/65
3- ተውሂድ አል አስማዕ ወስሲፋት
በቁርዓን እና ትክክለኛ በሆኑ የመልዕክተኛው ሀዲሶች ውስጥ የመጡትን የአላህ ስሞች እና ባህሪያት ከማንም ስሞችና ባህሪያት ጋር ሳያመሳስሉ፣ ቃሉን ሳያዛቡ፣ ትርጉማቸዉን ሳይለውጡ ወይም ሳያስተባብሉ ለአላህ እንደሚገቡ በማመን ማፅደቅ ማለት ነው፡፡ የአላህ ስሞች ብዙ ናቸዉ፡፡ ከነርሱም መሀከል ለምሳሌ አል-ራህማን፣ አል-ሰሚዕ፣ አል-በሲር፣ አል-አዚዝ እና አል ሀኪም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አላህ በአጠቃላይ በስሞቹ እና በባህሪዎቹ እሱን የሚመስል እንደሌለ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-
((لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ )) الشورى: ١١
(እንደርሱ ያለ ምንም ነገር የለም፤ እርሱ ሰሚዉና ተመልካቹ ነው) አል-ሹራ 11
አላህን በመስማትም ይሁን በመመልከት ባህሪያቱ ፍፁም የሚመስለዉ የለም፡፡ ይህ አንቀፅ የአላህን ባህሪያት ዉድቅ ለሚያደርጉትም ይሁን በባህሪያቱ ከፍጡራን ጋር ለሚያመሳስሉት ሰዎች ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ልንከተል የሚገባንን መርህ በሚገባ ቀርጿል፡፡አላህ እራሱን በገለፀባቸዉ ባህሪያቱ ስንገልፀዉ ከአምሳያ እናጠራዋለን!
[advanced-pdf-generator]