ተውሂዴ የነብያት ሁለ ጥሪ!

0
992

ተውሂድ ከዲን መሰረታዊ ከሆኑ ነገሮች በሙሉ ቅድሚያ ሊቸረው የቻለው አያሌ ጠቀሜታዎች ስላሉት ነው::ከነዚህም መካከል የሚከተሉት የጎላ ጠቀሜታዎች ይገኛሉ::

1.ተውሂድ በዱንያም ሆነ በ አኼራ ለሚከሰቱ ጭንቀቶችና ቅጣቶች መከላከያና መጠበቂያ ነው

2. በልቦናው ውስጥ ቅንጣት ታክል እንኳ ተውሂድ ኖሮት ወንጀሎችን ፈፅሞ የአላህ እዝነት ሳያገኘው ቀርቶ እሳት ቢገባ ግለሰቡ እሳት ውስጥ ዘውታሪ አይሆንም:: ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ልቦናው በተውሂድ የተሞላ ከሆነ በዱንያ ከጥመት የራቀ ይሆናል በ አኼራ ደግሞ ሙሉ ደህንነትን ያገኛል(እሳት ከነጭራሹ አይገባም)::

3. ተውሂድ የአላህን ውዴታንና ምንዳውን ለማግኘት ብቸኛው ሰበብ ነው::

4. ተውሂድን የያዘ ግለሰብ ብዙ አስከፊ ነገሮች ቢገጥሙትም እንኳ ከአላህ ውሳኔ መሆኑን በማመን በህይወቱ በጣም ደስተኛና የተረጋጋ ይሆናል::

5. ተውሂድን የያዘ ግለሰብ ለፍጠር ተገዥ ባሪያ አይሆንም::የሚፈራው:የሚከጅለው:ደጅ የሚጠናው ገታውን አንድ አላህን ብቻ ይሆናል::ይህ ነው የክብርና የልቅና መገለጫ!

6. ተውሂድን የያዘ ግለሰብ አላህ መጥፎ ከሚባል ነገር በሙሉ ሊጠብቀውና ጀነትን ሊያስገባው እንዲሁም በዚህች አለም እርሱን በማውሳት የመንፈስ እርካታን ሊያጎናፅፋቸው ቃል ገብቷል::

የነብያት ጥሪ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው

     ይህንን አጭር መልዕክት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ለማስተላለፍ ለረዳን አላህ ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ የአላህ ሰላትና ሰላም በመልዕክተኛው በቤተሰቦቻቸው እና በባልደረቦቻቸው ላይ ይሁን፡፡

አላህ እንዲህ ይላል ፡-

الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا ٥:٣

(ዛሬ ሀይማኖቻችሁን ሞላሁላችሁ፡፡ ፀጋዬንም በእናንተ ላይ ፈፀምኩ፡፡ ኢስላምንም ከሀይማኖት በኩል ለእናንተ ወደድኩ) አል ማዒዳህ 3

በዚህ አንቀጽ እንደተገለፀው የአላህ ዲን ሙሉ በሆነ መልኩ በመልዕክተኛው ﷺአማካኝነት ተላልፏል፡፡ ለኛ የሚበጅ ነገር ሆኖ ሳይጠቁሙን ያለፉት ነገር የለም፡፡   ከዓብዲላህ ኢብን ዓምር ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ የተከበሩት የአላህ መልዕክተኛ (ﷺ)  እንዲህ ይላሉ፡-

‹‹ለህዝቦቹ የሚያውቀውን መልካም ነገር መጠቆምና ከሚያውቅላቸው ክፉ ነገር ማስጠንቀቅ ግዴታ ቢሆንበት አንጂ ከእኔ በፊት (አንድም) ነቢይ አልነበረም›› ፡፡ 

ነብያት ይዘዋቸዉ ከመጡት መልዕክቶች ተቀዳሚ አጀንዳ አድርገዉ ያብራሩት በአላህ አንድነት ማመንና ብቸኛ ተመላኪነቱን ማረጋገጥ ተውሂድን ነዉ፡፡ ይህ የነብያት ፈለግ ነዉ፡፡ይህ ፈለጋቸዉ የሙስሊሞችን የዳእዋ አካሄድ የሚቀርፅ ነዉ፡፡ ትክክለኛ ዳዕዋ በዋነኝነት ከሚንቀሳቀስባቸው መሰረታዊ ነጥቦች መካከል ዋነኞቹ በተውሂድ በሱናና በዒልም የታነፀ ማህበረሰብ ማፍራት ነዉ፡፡

     እያንዳንዱ ሙስሊም ሊያውቃቸው የሚገቡ መሰረታዊ ቁርዓናዊና ሀዲሳዊ ትምህርቶችን በተከበሩት በመልዕክተኛው ባልደረቦች(ሰሀቦች) ግንዛቤ መረዳት ይገባዋል፡፡

 አላህ እኛን የፈጠረን በእርሱ ላይ ማንንም ሳናጋራ ልናመልከው ነው፡፡ ይህንንም ቀጥሎ ያለው አንቀፅ ይጠቁመናል፡፡

((وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ    (الذاريات: ٥٦)

(ጋኔንንም ይሁን ሰውን ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም) አልዛሪያት 56

የአላህም መልዕክተኛ (ﷺ)  ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ይህንኑ እዉነታ እንዲህ በማለት ይገልፁታል

((አላህ በባሮቹ ላይ ያለው መብት እርሱን ሊያመልኩት ከእርሱም ጋር ማንንም ላያጋሩ ነው፡፡)) 

አምልኮ (ዒባዳ)

ዒባዳ አላህ ለሚወዳቸው ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ንግግሮች እና ተግባሮች ሁሉ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ የአምልኮ ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ሰላት፣ ሩኩዕ፣ ሱጁድ ፣ እርድ(ዘብህ) ፣ ኹሹእ(መተናነስ)፣ መመካት፣ዱዓእ፣ፍራቻ(ኸዉፍ)፣ተስፋ ማድረግ (ረጃዕ)፣ ጠዋፍ እና መሐላ  እንዲሁም ሌሎች አላህ የደነገጋቸው የአምልኮ ዘርፎች ሁሉ ዒባዳ ይባላሉ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

قُلْ إِنَّ صَلَاتِي وَنُسُكِي وَمَحْيَايَ وَمَمَاتِي لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ الأنعام: ١٦٢

(ስግደቴ አምልኮቴም ህይወቴም ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው በል)አል-አንዓም162

የአላህ መልዕክተኛ (ﷺ)በሀዲሰል ቁድስ አላህ እንዲህ እንዳለ ይገልፃሉ ((ባሪያዬ እኔ ግዴታ ያደረግኩበትን ነገሮች ከመፈፀሙ በተሻለ ወደ እኔ የቀረበ የሚያደርገዉ ስራ የለም፡፡)) ቡኻሪ ዘግበዉታል

አላህ መልዕክተኞችን የላከው ወደ እርሱ አምልኮት እንዲጣሩና በእርሱ አምልኮ ላይ የሚፈፀም ሽርክን (ማጋራትን) እንዲያወግዙ ነው፡፡አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ  النحل: ٣٦

(በየህዝቡም ሁሉ ዉስጥ አላህን አምልኩ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልዕክተኞችን በእርግጥ ልከናል) አል ነህል 36

የአምልኮ የሚገነባባቸው መሰረቶች ሶስት ናቸው፡-

አንደኛ፡- ለተመላኪው በሙሉ ልብ መውደድ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَالَّذِينَ آمَنُوا أَشَدُّ حُبًّا لِّلَّهِ   البقرة: ١٦٥

‹‹እነዚያ ያመኑትም አላህን በመውደድ (ከነርሱ) ይበልጥ የበረቱ ናቸው፡፡›(አል በቀራህ 165)

ሁለተኛ፡- በሙሉ  ልብ መከጀል:: አላህ አንዲህ ይላል፡-

وَيَرْجُونَ رَحْمَتَهُ  الإسراء: ٥٧

‹‹እዝነቱንም ይከጅላሉ፡፡›› (አል ኢስራህ 57)

ሶስተኛ፡- በሙሉ  ልብ መፍራት:: አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَيَخَافُونَ عَذَابَهُ  الإسراء: ٥٧

‹‹ቅጣቱንም ይፈራሉ፡፡››(አል ኢስራህ 57

     አላህ እነዚህን ሶስት ታላላቅ መሰረቶች በፋቲሃ ምዕራፍ እንዲህ በማለት አካቷቻዋል፡፡

الْحَمْدُ لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ * الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ *  مَالِكِ يَوْمِ الدِّينِ  الفاتحة: ١ – ٤

‹‹ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለኾነው፤ እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ፡፡ የፍርዱ ቀን ባለቤት ለኾነው፡፡››(አል ፋቲሃ 1-3)

በመጀመሪያው አንቀጽ ውዴታ ተጠቅሷል፡፡ ምክንያቱም አላህ ባለ ውለታ ነው፡፡ ባለውለታ ደግሞ በዋለው ልክ ይወደዋል፡፡ በሁለተኛው አንቀጽ ክጀላ ተጠቁሟል፡፡ ሶስተኛው አንቀጽ ላይ ደግሞ ፍራቻ ተጠቅሷል፡፡ ምክንያቱም የምንዳና የመተሳሰብ ቀን ንጉስ ከቅጣቱ ይፈራል፡፡ ስለዚህም ነው አላህ በማስከተል እንዲህ ያለው  (إِيَّاكَ نَعْبُدُ) ማለትም የነዚህ ሶስቱ ባለቤት ጌታ ሆይ ይህ አንቀጽ(الْحَمْدُ لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ ) በሚጠቁመው ውዴታህ፣ ይህ አንቀጽ (الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ )በጠቆመው ክጀላህና ይህ አንቀጽ (مَالِكِ يَوْمِ الدِّينِ ) በጠቆመው ፍራቻህ አመልክሃለው ማለት ነው፡፡

አምልኮ በሁለት መሰፈርቶች እንጂ ተቀባይነት የለውም፦

1ኛ፡- አምልኮን ለተመላኪው ብቻ ለይቶ መስጠት፡፡ አላህ ለእርሱ ፊት ብቻ ጥርት የተደረገን ስራ እንጂ አይቀበልም፡፡ አላሀ እንዲህ ይላል፡-

وَمَا أُمِرُوا إِلَّا لِيَعْبُدُوا اللَّهَ مُخْلِصِينَ لَهُ الدِّينَ  البينة: ٥

‹‹የአላህን ሃይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች፣ ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት… እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)፡፡›› (አል በይነህ 5)

أَلَا لِلَّهِ الدِّينُ الْخَالِصُ الزمر: ٣

‹‹ንቁ! ፍጹም ጥሩ የኾነው ሃይማኖት የአላህ ብቻ ነው፡፡›› (ዙመር 3)

قُلِ اللَّهَ أَعْبُدُ مُخْلِصًا لَّهُ دِينِي  الزمر: ١٤

አላህን «ሃይማኖቴን ለእርሱ ያጠራሁ ኾኜ እግገዛዋለሁ» በል፡፡ (ዙመር 14)

2ኛ፡- መልዕክተኛውን (ﷺ)  ተከታይ መሆን፡፡ አላህ ማንኛውም ስራ የመልዕክተኛውን (ﷺ)  መመሪያ ያልተስማማ ከሆነ አይቀበልም፡፡  አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا  الحشر: ٧

‹‹መልክተኛውም የሰጣችሁን (ማንኛውንም) ነገር ያዙት፡፡ ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ፡፡›› (አል ሀሽር7)

 فَلَا وَرَبِّكَ لَا يُؤْمِنُونَ حَتَّىٰ يُحَكِّمُوكَ فِيمَا شَجَرَ بَيْنَهُمْ ثُمَّ لَا يَجِدُوا فِي أَنفُسِهِمْ حَرَجًا مِّمَّا قَضَيْتَ وَيُسَلِّمُوا تَسْلِيمًا  النساء: ٦٥

‹‹በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፤ (ምእመን አይኾኑም)፡፡››(አል ኒሳህ 65)

ነብዩም (ﷺ)  እንዲህ ብለዋል

{من أحدث في أمرنا هذا ما ليس منه فـهو رد}

‹‹በዚህ ዲናችን ውሰጥ ከሱ ያልሆነን አዲስ ነገር የፈጠረ ስራው ተመላሽ ነው፡፡››

ለአላህ ብቻ በመለየት ያልተሰራና ትክክለኛ ያልሆነ ስራ ትርጉም የለውም፡፡

    እነዚህን ሁለት መስፈርቶች አካተው ከያዙ አንቀፆች ውሰጥ የሚከተለው በአል ከህፍ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የተወሳው የአላህ ቃል አንዱ ነው፡፡

قُلْ إِنَّمَا أَنَا بَشَرٌ مِّثْلُكُمْ يُوحَىٰ إِلَيَّ أَنَّمَا إِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌ وَاحِدٌ ۖ فَمَن كَانَ يَرْجُو لِقَاءَ رَبِّهِ فَلْيَعْمَلْ عَمَلًا صَالِحًا وَلَا يُشْرِكْ بِعِبَادَةِ رَبِّهِ أَحَدًا  الكهف: ١١٠

«እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደኔ የሚወረድልኝ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ፡፡ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፡፡ በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ» በላቸው፡፡ (አል ከህፍ 11ዐ)

ተውሂድ

አላህን በጌትነቱ በብቸኛ ተመላኪነቱ በስሞቹ እና በባህሪያቱ ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ተውሂድ በ ሦስት የሚከፈል ሲሆን  እነሱም፡

  1. ተውሂደ አል-ሩቡቢያህ:- አላህን በስራዎቹ አንድ ማድረግ፡፡ ይህም ማለት፤ መፍጠር፣ሲሳይን መስጠት፣ነገሮችን ማስተናበር፣ መግደል እና ህያው ማድረግ በመሳሰሉት ድርጊቶቹ አላህን ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡

ከአላህ ሌላ ፈጣሪ የለም፡፡ አላህ ይህንን እንዲህ በማለት ይገልፅልናል፡-

اللَّهُ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ ۖ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ الزمر: ٦٢

(አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው) አል-ዙመር 62

ከአላህ ሌላ ሲሳይን የሚሰጥ የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَمَا مِن دَابَّةٍ فِي الْأَرْضِ إِلَّا عَلَى اللَّهِ رِزْقُهَا وَيَعْلَمُ مُسْتَقَرَّهَا وَمُسْتَوْدَعَهَا ۚ كُلٌّ فِي كِتَابٍ مُّبِينٍ هود: ٦

(በምድርም ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለም ሲሳዩ አላህ ዘንድ ያለ ቢሆን እንጂ)  ሁድ 6

ከአላህ ሌላ ነገሮችን የሚያስተናብር የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-

 يُدَبِّرُ الْأَمْرَ مِنَ السَّمَاءِ إِلَى الْأَرْضِ السجدة: ٥

 (ነገርን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያስተናብራል)    አል-ሰጅዳህ 5

ከአላህ ሌላ ህያው ሊያደርግ እንዲሁም ሊገድል የሚችል የለም፡፡ ይህንን በማስመልከት አላህ እንዲህ ይላል፡-

هُوَ يُحْيِي وَيُمِيتُ وَإِلَيْهِ تُرْجَعُونَ  يونس: ٥٦

(እርሱ ህያው ያደርጋል ይገላልም ወደርሱም ትመለሳላችሁ) ዩኑስ 56 

ይህን ዓይነቱን የተውሂድ ክፍል በረሱል ዘመን የነበሩ ከሀዲያን አጋሪዎች ያልካዱት ቢሆንም ከባዕድ አምልኮ ባለመላቀቃችዉ ወደ ኢስላም ሊያስገባቸው አልቻለም፡፡ አላህም ይህን የተውሂድ ክፍል ማረጋገጣቸውን በማስመልከት እንዲህ ይላል፡-

وَلَئِن سَأَلْتَهُم مَّنْ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ لَيَقُولُنَّ اللَّهُ  لقمان: ٢٥

(ሰማያትና ምድርንም የፈጠረ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይላሉ)ሉቅማን 25

2- ተውሂድ አል-ኡሉሂያህ

አላህን  በአምልኮ አንድ ማድረግ፡፡ በዱዓእ (ልመና)፣ በፍራቻ፣በመመካት፣እርዳታን እና ጥበቃን በመጠየቅ እንዲሁም እርሱ ባሮቹን ባዘዘባቸው ሌሎች አምልኮቶች ሁሉ ብቸኛ ማድረግ ማለት ነው፡፡ የአምልኮ ዓይነቶችን ሁሉ ያለምንም አጋር ለርሱ ብቻ ማድረግን ግዴታ ያደርጋል፡፡

ከአላህ ሌላ ማንንም አንለምንም፡፡ አላህ እርሱን ብቻ መለመን እንዳለብን ሲነግረን እንዲህ ይላል፡-

وَقَالَ رَبُّكُمُ ادْعُونِي أَسْتَجِبْ لَكُمْ  غافر: ٦٠

(ጌታችሁም አለ! ለምኑኝ እቀበላችኃለሁና)  አል-ጋፊር  60    

ከአላህ ሌላ አምልኮታዊ የሆነ ፍራቻን ማንንም ቢሆን አንፈራም፡፡ አላህ  እንዲህ ይለናል፡-

فَلَا تَخَافُوهُمْ وَخَافُونِ إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ  عمران: ١٧٥

(አትፍሯቸውም አማኞች የሆናችሁ እንደሆነ {እኔን ብቻ} ፍሩኝ) አል-ኢምራን175

ከአላህ ሌላ በማንም አንመካም፡፡ አላህ አማኞች በእርሱ ላይ ብቻ ሊመኩ እንደሚገባ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-

وَعَلَى اللَّهِ فَتَوَكَّلُوا إِن كُنتُم مُّؤْمِنِينَ  المائدة: ٢٣

(አማኞች እንደሆናችሁ በአላህ ላይ ብቻ ተመኩ) አል-ማዒዳህ 23

  • ከአላህ ሌላ ፍጡራን በማይችሉት ጉዳይ ላይ እርዳታን ከአላህ ዉጪ ከማንም አንጠይቅም፡፡ ይህን በማስመልከት አላህ በሱረቱል ፋቲሀ ላይ ደጋግመን ምናነባቸዉን አንቀፆች አዉርዷል፡፡

إِيَّاكَ نَعْبُدُ وَإِيَّاكَ نَسْتَعِينُ  الفاتحة: ٥

(አንተን ብቻ እናመልካለን፤ ከአንተም ብቻ  እርዳታ እንጠይቃለን) አል-ፋቲሀ 5

  • ከአላህ ሌላ ከማንም ጥበቃን አንጠይቅም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

 قُلْ أَعُوذُ بِرَبِّ النَّاسِ  الناس: ١

የሰዎች ጌታ በሆነው እጠበቃለሁ በል) አል-ናስ 1

 ይህ የተውሂድ ክፍል የአላህ መልዕክተኞች ለሰው ልጆች ለማስተላለፍ ከአላህ ይዘው የመጡት ዋነኛው መልዕክት ነው፡፡ ሁሉም ነብያቶቸ የዳዕዋቸዉ ዋና ተልዕኮ አምልኮን ባጠቃላይ ለአላህ ብቻ ማድረግ (ተውሂደል ኡሉሂያህ) ነው፡፡ ይህንን አላህ በቀጣዩ አንቀፅ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡፡ 

وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ  النحل: ٣٦

(በየህዝቡም ሁሉ ዉስጥ አላህን አምልኩ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልዕክተኞችን በእርግጥ ልከናል) አል ነህል 36

ይህንኑ የተውሂድ ክፍል እና የነብያቶች መልዕክት ነዉ የፊተኞቹ ሆኑ በዘመናችን የሚገኙ አጋሪዎች ያስተባበሉት፡፡ የመካ ሙሽሪኮች መልዕክተኛው አንድን አምላክ ብቻ አምልኩ ባሏቸው ጊዜ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ አላህ እንዲህ ይላል፡-

أَجَعَلَ الْآلِهَةَ إِلَٰهًا وَاحِدًا ۖ إِنَّ هَٰذَا لَشَيْءٌ عُجَابٌ  ص: ٥

(አማልክቶቹን አንድ አምላክ አደረጋቸዉን? ይህ አስደናቂ ነገር ነውአሉ) ሷድ 5 

አላህ በየዘመናቱ ከላካቸው ነብያት (ኑህ፣ሁድ፣ሳልህ እና ሹዓይብ) ጥሪ ይህን ይመስል እንደነበር በተለያዩ አንቀፆች ገልፆልናል፡-

 ((يَا قَوْمِ اعْبُدُوا اللَّهَ مَا لَكُم مِّنْ إِلَٰهٍ غَيْرُهُ ))

(ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ ከእርሱ በቀር ምንም አምላክ የላችሁም…)

አል-አእራፍ 59/65/73/85

3- ተውሂድ አል አስማዕ ወስሲፋት

     በቁርዓን እና ትክክለኛ በሆኑ የመልዕክተኛው ሀዲሶች ውስጥ የመጡትን የአላህ ስሞች እና ባህሪያት ከማንም ስሞችና ባህሪያት ጋር ሳያመሳስሉ፣ ቃሉን ሳያዛቡ፣ ትርጉማቸዉን ሳይለውጡ ወይም ሳያስተባብሉ ለአላህ እንደሚገቡ በማመን ማፅደቅ ማለት ነው፡፡ የአላህ ስሞች ብዙ ናቸዉ፡፡ ከነርሱም መሀከል ለምሳሌ አል-ራህማን፣ አል-ሰሚዕ፣ አል-በሲር፣ አል-አዚዝ እና አል ሀኪም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አላህ በአጠቃላይ በስሞቹ እና በባህሪዎቹ እሱን የሚመስል እንደሌለ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-

لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ   الشورى: ١١

(እንደርሱ ያለ ምንም ነገር የለም፤ እርሱ ሰሚዉና ተመልካቹ ነው) አል-ሹራ 11

አላህን በመስማትም ይሁን በመመልከት ባህሪያቱ ፍፁም የሚመስለዉ የለም፡፡ ይህ አንቀፅ የአላህን ባህሪያት ዉድቅ ለሚያደርጉትም ይሁን በባህሪያቱ ከፍጡራን ጋር ለሚያመሳስሉት ሰዎች ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ልንከተል የሚገባንን መርህ በሚገባ ቀርጿል፡፡አላህ እራሱን በገለፀባቸዉ ባህሪያቱ ስንገልፀዉ ከአምሳያ እናጠራዋለን!!

ሽርክ

በአምልኮ ከአላህ ጋር ሌላን  እኩል ማድረግ ማለት ነዉ፡፡ አምልኮን ከአላህ ዉጪ ለማንም ማዋል የሽርክ ተግባር ነዉ፡፡ ተዉሂድ ፍትህ ነዉ፡፡ ሽርክ ግን የበደሎች ሁሉ በደል ነዉ፡፡ በመሆኑም አላህ የማይምረዉ ከባድ ወንጀል ነዉ፡፡

  إِنَّ اللَّهَ لَا يَغْفِرُ أَن يُشْرَكَ بِهِ وَيَغْفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَاءُ   النساء : ٤٨

አላህ በእርሱ ላይ ማጋራትን (ሽርክን) በፍፁም አይምርም! ከሽርክ በታች ያለን (ኃጢአት) ለሚሻው ሠው ይምራል”  አል-ኒሳዕ 48

   አንዳንድ ሰዎች ስለ ተውሂድ መስማት አይፈልጉም፡፡ የተለያዩ የኢባዳ አይነቶችን ለነብያት ፣ ለመላዕክት እና ለሷሊሆች ያዉላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ጭንቅ በሚገጥማቸዉ ጊዜ በቀብር ዙሪያ ጠዋፍ ያደርጋሉ፣ ከአላህ ዉጪ ማንም መፈፀም የማይችላቸዉን ጉዳዮች ለማስፈፀም ከምዕተ አመታት በፊት ለኖሩ  ሰዎች የድረሱልን ጥሪ ያሰማሉ! ይማፀናሉ!! ልጅ ቢያጡ ለሚያመልኩት ሰዉ ስለት ይገባሉ፣ በስሙም ይምላሉ፡፡ በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች ይህ አይነቱ ቀብር አምልኮ ሰዎችን እየሸነገለ ይገኛል፡፡

ጁንዱብ ኢብኑ አብዲላህ ባስተላለፉት ሀዲስ ነብዩ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡-

(አደራችሁን! ቀብሮችን የአምልኮ ስፍራ አንዳታረጉ፡፡ እኔ ከዚህ አይነቱ ተግባር እከለክላችለሁ፡፡) ሙስሊም ዘግበዉታል

     አዎ! ታላቁ ነብይ ይህንን የተናገሩት ህይወታችዉ ከማለፉ አምስት ቀናት ብቻ ቀደም ብለዉ ነበር፡፡ ደግመዉ ደጋግመዉ ተመሳሳይ መልዕክት አስተምረዋል፡፡ በዱንያ ቆይታቸዉ በመጨረሻዎቹ ሰዓታት ሳይቀር ከቀብር አምልኮ አስጠንቅቀዋል፡፡ አጅግ በጣም የሚያሳዝነዉ፤ ሸይጣን ይህ አይነቱን ባዕድ አምልኮ የሚያስፋፋበትን ስልት መቀየሩ ነዉ፡፡አንዳንድ ሰዎች ‹ቅርስን መንከባከብ› ፣  ‹ታሪክን ማቆየት› እና መሰል ምክኒያቶችን በማቅረብ የቀብር አምልኮ ቦታዎች በብዙ ወጪ እያሻሻሉና እየገነቡ ይገኛል፡፡ ይህ አይነቱ ተግባር ባዕድ አምልኮን ያበረታታል፡፡ በቁርአንና በሱና የተጠቀሱ መረጃዎች አጅግ በጣም ግልፅና በርካታ ከመሆናቸዉ ጋር የተለያዩ ጦሪቃዎን የሚከተሉ ሙሪዶች አንዲያዉቋቸዉ አልተደረገም፡፡ አንድ ዒባዳ(አምልኮ) ተቀባይነት እንዲያገኝ ሁለት መስፈርቶች መሟላት አለባቸዉ፡፡ በኢኽላስ ለአላህ ብቻ ሊፈፀም እና በነብዩ የአምልኮ ፈለግ መሰረት ሊተገበር ይገባዋል፡፡

 አላህ ቀጥተኛዉን መንገድ ሁላችንንም ይመራን ዘንድ እንማፀነዋለን!! 

በ PDF Download(ዳውንሎድ)ለማድረግ