በተወረዱ መፅሐፍት ማመን

0
113

የወህይ ቋንቋዊና ሸሪዓዊ ትርጉምና አይነቶቹ ቋንቋዊ ትርጉሙ

ወህይ ቋንቋዊ ትርጓሜው ስውር የሆነ ፈጣን ዜና ማለት ሲሆን ወህይ ምልክት፣ ፅሁፍ መልክትና አሳዋቂ መንፈስ የሚል ትርጉምም ይሰጣል፡፡

በየትኛው አይነት መንገድ ወደ ሰዎች ልከህ እንዲገነዘቡ ያደረከው ነገር ሁሉ ወህይ ሊባል ይችላል፡፡ ስለዚህ ወህይ ከአላህ በመሆን ወይም ወደ ነቢያት የሚደርን በመሆን ብቻ አይገደብም፡፡ በዚህ መሰረት ወህይ ቋንቋዊ ትርጉሙ የሚከተሉትን ያካትታል፡-

  1. ተፈጥሯዊ አሳዋቂ መንፈስ ለዚህኛው አይነት ወህይ የሙሳ እናት ወህይ ምሳሌ ይሆናል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል

{ وَأَوْحَيْنَا إِلَى أُمِّ مُوسَى أَنْ أَرْضِعِيهِ } (القصص : 7)

‹‹ወደ ሙሳም እናት «አጥቢው … ማለትን አመለከትን፡፡›› ቀሰስ 7

  1. ለንቦች የተደረገው አይነት ለእንስሳዎች የሚደረግ ተፈጥሯዊ አሳዋቂ መንፈስ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል

 { وَأَوْحَى رَبُّكَ إِلَى النَّحْلِ أَنِ اتَّخِذِي مِنَ الْجِبَالِ بُيُوتًا } (النحل : 68)

‹‹ጌታህም ወደ ንብ እንዲህ ሲል አስታወቀ «ከተራራዎች፣ ከዛፍም፣ (ሰዎች) ከሚሠሩትም (ቀፎ) ቤቶችን ያዢ፡፡›› ነህል 48

  1. ዘከሪያ ለህዝቦቹ ያደረገው አይነት ጥቆማ አዘል ቅብብታዊ ምልክት፡፡ አላህ እንዲህ ይላል

{ فَخَرَجَ عَلَى قَوْمِهِ مِنَ الْمِحْرَابِ فَأَوْحَى إِلَيْهِمْ أَنْ سَبِّحُوا بُكْرَةً وَعَشِيًّا } (مريم : 11)

‹‹ከምኩራቡም በሕዝቦቹ ላይ ወጣ፡፡ በ×ትና በማታ (ጌታችሁን) አወድሱ በማለትም ወደነሱ ጠቀሰ፡፡›› መርየም 11

  1. አሸብራቂ ማቃለያ የሆነ የሸይጠን ውትወታ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል

{ وَإِنَّ الشَّيَاطِينَ لَيُوحُونَ إِلَى أَوْلِيَائِهِمْ لِيُجَادِلُوكُمْ } (الأنعام : 121)

  1. መላኢካች እንደፈፀሙት የሚታዘዙት የአላህ ትዕዛዝ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል

{ إِذْ يُوحِي رَبُّكَ إِلَى الْمَلَائِكَةِ أَنِّي مَعَكُمْ فَثَبِّتُوا الَّذِينَ آمَنُوا } (الأنفال : 12)

‹‹ጌታህ ወደ መላእክቱ «»እኔ (በእርዳታዬ) ከእናንተ ጋር ነኝና እነዚያን ያመኑትን አጽናኑ፡፡›› አል አንፋል 12

ሸሪዓዊ ትርጉሙ

የወህይ ሸሪዓዊ ትርጓሜ እንደሚከተለው ይገለፃል፡- “አላህ ወደ ነቢያት በመላኢካ አማካኝነት ወይም በቀጥታ የሚያስተላልፈው ህግጋት ወይም መፅሐፍ፡፡”

የወህይ አይነቶች

የወህይ አቀባበል በሶስት አይነት ደረጃዎች የሚከፋፈል መሆኑን አላህ ሱረቱ ሹራ ላይ እንዲህ ሲል ገልፃል

وَمَا كَانَ لِبَشَرٍ أَنْ يُكَلِّمَهُ اللَّهُ إِلَّا وَحْيًا أَوْ مِنْ وَرَاءِ حِجَابٍ أَوْ يُرْسِلَ رَسُولًا فَيُوحِيَ بِإِذْنِهِ مَا يَشَاءُ إِنَّهُ عَلِيٌّ حَكِيمٌ } (الشورى : 51)

‹‹ለሰውም አላህ በራእይ፣ ወይም ከግርዶ ወዲያ፣ ወይም መልክተኛን (መልአክን) የሚልክና በፈቃዱ የሚሻውን ነገር የሚያወርድለት ቢኾን እንጅ (በገሃድ) ሊያናግረው ተገቢው አይደለም፡፡ እርሱ የበላይ ጥበበኛ ነውና፡፡›› ሹራ 51

አንደኛ ደረጃ፡- በቀጥታ አላህ ሊያሳውቀው የሚፈልገው ሰው ልብ ላይ የሚያርፍ መንፈስ ሲሆን ከአላህ ለመሆኑ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የማይሰጠው ይሆናል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው አብደላህ ኢብን መስዑድ ያስተላለፉት ሀዲስ ነው፡፡ ነብዩ ሰዐወ እንዲህ አሉ

« إن روح القدس نفث في روعي لن تموت نفس حتى تستكمل رزقها فاتقوا الله وأجملوا في الطلب »

“ቅዱስ መንፈስ እያንዳንዷ ነፍስ የተመደበላትን ሲሳይ ሳትፈፅም አትሞትም” የሚል መልዕክት ልቤ ላይ አሳርፏልና አላህን ፈርታችሁ ስራችሁን አሳምሩ፡፡”[መዋሪድ ዘምአን 1ዐ84፣ 1ዐ85 ሙስተድረክ 2/4 ኢብን ማጃህ 2144]

አንዳንድ ዑለማዎች የነቢያትን ህልም ከዚኛው ክፍል ውስጥ ያካትቱታል፡፡ ለምሳሌ የነብዩ ኢብራሂም ህልም

{ قَالَ يَا بُنَيَّ إِنِّي أَرَى فِي الْمَنَامِ أَنِّي أَذْبَحُكَ } (الصافات : 102)

«ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ እኔ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ?» አለው፡፡ ሷፋት 1ዐ2

እንዲሁ ነብዩ ሰዐወ የነቢይነት ጅማሪያቸው ላይ ሲያዩት የነበረውን ህልም፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም በአስተላለፉት ሀዲስ ዓኢሻ እንዲህ ብለዋል

« أول ما بدئ به رسول الله صلى الله عليه وسلم من الوحي الرؤيا الصالحة في النوم فكان لا يرى رؤيا إلا جاءت مثل فلق الصبح »
“የአላህ መልዕክተኛ ወህይን መቀበል የጀመሩበት በመልካም ህልም ነበር፡፡ የሚያዩት ህልም እንደ ንጋት ብርሃን ግልፅ ሆኖ ይመጣ ነበር…”[ቡኻሪ 3 ሙስሊም 16ዐ]

ሁለተኛ ደረጃ፡- አንዳንድ ነቢያትን ከመጋረጃ በስተጀርባ ያለምንም አማካይ በቀጥታ ማናገር፡፡

ይህኛው አይነቱ ወህይ አላህ ነቢዩ ሙሳን የሚያናግርበት እንደነበር በቁርአን በተለያዩ ቦታዎች ሰፍሯል፡፡

{ وَكَلَّمَ اللَّهُ مُوسَى تَكْلِيمًا } (النساء : 164)

‹‹አላህም ሙሳን ማነጋገርን አነጋገረው፡፡›› አል ኒሳእ 164

{ وَلَمَّا جَاءَ مُوسَى لِمِيقَاتِنَا وَكَلَّمَهُ رَبُّهُ } (الأعراف : 143)

‹‹ሙሳም ለቀጠሯችን በመጣና ጌታውም ባነጋገረው ጊዜ…›› አል አዕራፍ 143

አደምንም በዚህ መልኩ አናግሯል

{ فَتَلَقَّى آدَمُ مِنْ رَبِّهِ كَلِمَاتٍ } ( البقَرة : 37)

‹‹አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡››  አል በቀራህ 37

ነብዩንም ሰዐወ በዚህ መልኩ የኢስራእ ሌሊት እንዳናገራቸው በሀዲስ ተጠቅሷል፡፡

ሶስተኛ ደረጃ፡- በመልአክ አማካኝነት ወህይ ማስተላለፍ፡፡ ይህ ደግሞ ጅብሪል ከአላህ ወደ ነብያት የሚያስተላልፈው የወህይ አይነት ነው፡፡ አላህ አንዲህ ይላል

{ أَوْ يُرْسِلَ رَسُولًا فَيُوحِيَ بِإِذْنِهِ مَا يَشَاءُ } (الشورى : 51)

‹‹ወይም መልክተኛን (መልአክን) የሚልክና በፈቃዱ የሚሻውን ነገር የሚያወርድለት ቢኾን እንጅ …›› ሹራ 51

ቁርአን ሁሉም በዚህ መልኩ የአላህን ንግግር ጅብሪል በመስማት ወደ ነብዩ ሰዐወ ያስተላለፈው ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል

{ وَإِنَّهُ لَتَنْزِيلُ رَبِّ الْعَالَمِينَ }{ نَزَلَ بِهِ الرُّوحُ الْأَمِينُ }{ عَلَى قَلْبِكَ لِتَكُونَ مِنَ الْمُنْذِرِينَ } (الشعراء : 192- 194)

እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡ እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤ ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡ ›› ሹዐራእ 192-194

{ قُلْ نَزَّلَهُ رُوحُ الْقُدُسِ مِنْ رَبِّكَ بِالْحَقِّ } (النحل : 102)

‹‹(ቁርኣንን) ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው በላቸው፡፡›› አል ነህል 1ዐ2

ጅብሪል ወደ ነቢያችን ወህይን ሲያደርስ በሶስት አይነት ሁኔታዎች ነው፡፡

  1. ነብዩ ሰዐወ በተፈጠረበት መልኩ እያዩት ሲሆን ነገር ግን ይህ ሁኔታ የተከሰተው ክፍል አንድ ላይ እንደተጠቀሰው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡
  2. በቃጭል ድምፅ መልኩ ወደ ነቢዩ ይስተላለፍና በሚገባ ከያዙት በኃላ ይወገዳል፡፡
  3. በወንድ ልጅ መልክ ተመስሎ ይመጣና በንግግር ወህዩን ያስተላልፋል፡፡

ስለሁለተኛውና ሶስተኛው ሁኔታዎች ነብዩ ሰዐወ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል

(أحيانا يأتيني مثل صلصلة الجرس ، وهو أشده علي ، فيفصم عني وقد وعيت عنه ما قال . وأحيانا يتمثل لي الملك رجلا فيكلمني فأعي ما يقول »

“አንዳንዴ በቅጭል ድምፅ መልኩ ይመጣኛል፡፡ ይህ ግን ከባዱ ሁኔታ ነው ለቆኝ ሲሄድ ያለኝን በሚገባ ሸምድጄ አገኘዋለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ መልአኩ በሰው ምስል ይሆንና ያናግረኛል እኔም የሚለኝን በሚገባ እይዛለሁ፡፡”[ቡኻሪ 2 ሙስሊም 2333]