በቅስቀሳ ማመን ከታላላቅ የእምነት መሰረቶች አንዱ ነው፡፡ በቅስቀሳ ማመን በውስጡ ብዙ ነገሮችን እንድናይ ስለሚጋብዝ በስምንት ነጥቦች ከፋፍለን ለማየት እንሞክራለን፡፡
አንደኛ፡- ቅስቀሳ ምንድ ነው?
ቅስቀሳ ሲባል ሙታን ህያው ሆነው ከቀብር መውጣታቸን ነው፡፡ አላህ በችሎታው የሙታን አካል ካለቀ በኃላ እንዲሰበሰብ ያደርግና ከነፍሶቿ ጋር በማገናኘት ወደ ፍርድ ቦታ እንዲሰበሰቡ ያደርጋል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል
{ وَضَرَبَ لَنَا مَثَلًا وَنَسِيَ خَلْقَهُ قَالَ مَنْ يُحْيِي الْعِظَامَ وَهِيَ رَمِيمٌ }{ قُلْ يُحْيِيهَا الَّذِي أَنْشَأَهَا أَوَّلَ مَرَّةٍ وَهُوَ بِكُلِّ خَلْقٍ عَلِيمٌ } (يس : 78 ، 79)
ለእኛም ምሳሌን አደረገልን፡፡ መፈጠሩንም ረሳ፡፡ «አጥንቶችን እነርሱ የበሰበሱ ሲኾኑ ሕያው የሚያደርጋቸው ማነው?» አለ፡፡ «ያ በመጀመሪያ ጊዜ (ከኢምንት) ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል፡፡ እርሱም በፍጡሩ ሁሉ (ኹኔታ) ዐዋቂ ነው» በለው፡፡ (ያሲን 78-79)
ሁዘይፋ በአስተላለፉት ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ ሰዐወ እንዲህ ብለዋል “በአንደ ወቅት አንድ ሰው ከህይወት ተስፋ ቆርጦ እንደሚሞት ሲያውቅ ለቤተሰቦቹ አንዲህ ሲል ተናዘዘ “ስሞት እንጨት አቀጣላችሁ አካሌን እሳት ውስጥ ክተቱና እሳቷን ስጋዬን በልታ አጥንቴ ጋር ስትደርስ አጥንቴን ፈጭታችሁ በነፋሻ ቀን በትኑት” አላህም ይህን አካል ሰብስቦ ከቀሰቀሰው በኃላ “እንዴት እንዲህ ልታደርግ ቻልክ” ሲል ጠየቀው እሱም “አንተን ፈርቼ” ሲለለው ኃጢአቱን ማረው፡፡”[1]
ቅስቀሳ በምን መልኩ እንደሆነ አቡ ሐይራ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ ሰዐወ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል “በሁለቱ (የመግደልና የመቀስቀሻ) ንፊዎች መካከል አርባ ጊዜ አለ (አቡ ሑረይራ አርባ አመት ወይም ወራት ወይም ቀናት መሆኑን አልገለፁም) ከዚያ አላህ ከሰማይ ያዘንብና ልቅ ቡቃያ እንደሚበቅለው ሙታን ይበቅላሉ፡፡ ከሰው ልጅ ወገቡ ላይ ትንሽ አጥንት በስተቀርር ሁሉም መሬት የሚበላው ሲሆን የቂያማ እለት የሚበቅሉት ከዚያች አጥንት ነው፡፡”[2]
ሁለተኛ፡- መቀስቀስ እንዳለ የቁርአን የሀዲስና የአእምሮ ማስረጃዎች
ከቁርአን ማስረጃዎች
አላህ እንዲህ ብሏል
{ ثُمَّ بَعَثْنَاكُمْ مِنْ بَعْدِ مَوْتِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ } (البقرة : 56)
‹‹ከዚያም ታመሰግኑ ዘንድ ከሞታችሁ በኋላ አስነሳናችሁ፡፡›› አል በቀራህ 56
{ مَا خَلْقُكُمْ وَلَا بَعْثُكُمْ إِلَّا كَنَفْسٍ وَاحِدَةٍ إِنَّ اللَّهَ سَمِيعٌ بَصِيرٌ } (لقمان : 28)
‹‹እናንተን መፍጠርና እናንተን መቀስቀስ እንደ አንዲት ነፍስ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ አላህ ሰሚ ተመልካች ነውና፡፡›› ሉቅማን 28
{ زَعَمَ الَّذِينَ كَفَرُوا أَنْ لَنْ يُبْعَثُوا قُلْ بَلَى وَرَبِّي لَتُبْعَثُنَّ ثُمَّ لَتُنَبَّؤُنَّ بِمَا عَمِلْتُمْ وَذَلِكَ عَلَى اللَّهِ يَسِيرٌ } (التغابن : 7)
እነዚያ የካዱትን በፍጹም የማይቀሰሱ መኾናቸውን አሰቡ፡፡ «አይደለም በጌታዬ እምላለሁ፡፡ በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ፡፡ ከዚያም በሠራችሁት ሁሉ ትነገራላችሁ፡፡ ይህም በአላህ ላይ ቀላል ነው፡፡» በላቸው፡፡ (ተጋቡን 7)
ከሀዲስ ማስረጃዎች
አቡ ሑረይራ እንዳስተላለፉት ነቢዩ ሰዐወ እንዲህ ብለዋል
« لا تفضلوا بين أنبياء الله فإنه ينفخ في الصور فيصعق من في السماوات ومن في الأرض إلا من شاء الله قال : ثم ينفخ فيه مرة أخرى فأكون أول من بعث أو في أول من بعث فإذا موسى آخذ بالعرش »
“በነቢያት መካከል (ለፉክክር) አታበላልጡ በቀንድ ሲነፋ አላህ የፈለገው ስቀር በሰማይና ምድር ውስጥ ያለ ሁሉ ይሞታል ከዚያ ለሁለተኛ ሲነፋ መጀመሪያ እቀሰቀሳለሁ ነገር ግን ሙሳ ዓርሽን ይዞ አየዋለሁ፡፡”[3]
አቡ ሰዒድ አልኹድሪ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ ሰዐወ “የመጀመሪያው መሬት የሚከፈትለት ሰው እሆናለሁ፡፡”[4] እነዚህ ሁለት ሀዲሶች ሰዎች የቂያማ እለት ከቀብራቸው እንደሚቀሰቀሱና ነቢዩም ሰዐወ የመጀመሪያው ተቀስቃሽ በመሆን ብልጫ እንዳላቸው ነው፡፡
የአእምሮ ማስረጃ
ጤናማ አእምሮ መፍጠር የቻለ ጌታ የሞተን ደግሞ ህያው ማድረግ እንደማያቅተው ያረጋግጣል፡፡ አላህ ከሞት በኃላ መቀስቀስ ከባድና የማይቻል አድርጎ ለሚያስብ እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጥቶታል፡፡
{ مَنْ يُحْيِي الْعِظَامَ وَهِيَ رَمِيمٌ } (يس : 78) ، قال تعالى : { قُلْ يُحْيِيهَا الَّذِي أَنْشَأَهَا أَوَّلَ مَرَّةٍ } (يس : 79)
በሌላም አንቀፅ እንዲህ ይላል
{ وَهُوَ الَّذِي يَبْدَأُ الْخَلْقَ ثُمَّ يُعِيدُهُ وَهُوَ أَهْوَنُ عَلَيْهِ } (الروم : 27)
ሶስተኛ፡- ለፍርድ መሰብሰብ
የቁርአንና የሀዲስ መረጃዎች የቂያማ እለት ሰዎች ያለጫማ በእርቃናቸው ሳይገረዙ በአንድ ቦታ ላይ እንደሚሰበሰቡ አብራርተው ገልፀዋል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል
{ وَحَشَرْنَاهُمْ فَلَمْ نُغَادِرْ مِنْهُمْ أَحَدًا } (الكهف : 47)
‹‹እንሰበስባቸዋለንም፡፡ ከእነሱም አንድንም አንተውም፡፡›› ከህፍ 47
{ يَوْمَ تُبَدَّلُ الْأَرْضُ غَيْرَ الْأَرْضِ وَالسَّمَاوَاتُ وَبَرَزُوا لِلَّهِ الْوَاحِدِ الْقَهَّارِ } (إبراهيم : 48)
‹‹ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበትን ሰማያትም (እንደዚሁ) አንድ አሸናፊ ለኾነው አላህም (ፍጡራን ሁሉ) የሚገለጹበት ቀን (አስታውሱ)፡፡›› ኢብራሂም 48
አኢሻ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ ሰዐወ እንዲህ ብለዋል
« يحشر الناس يوم القيامة حفاة عراة غُرْلا (1) ) قلت : يا رسول الله! النساء والرجال جميعًا ، ينظر بعضهم إلى بعض ؟ قال صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلِّم : (يا عائشة الأمر أشد من أن ينظر بعضهم إلى بعض »
“የቂያማ እለት ሰዎች ያለጫማ እርቃናቸውን ሳይገረዙ ይሰበሰባሉ” አዒሻም ለነቢዩ ሰዐወ “የአላህ መልዕክተኛ ሆይ ወንድም ሴቱም አንድ ላይ እየተያዩ?” ሲሉ ጠየቋቸው ነቢዩ ሰዐወ እንዲህ ሲሉ መለሱ “አዒሻ ሆይ ነገሩ ከባድ በመሆኑ አንዱ ሌላውን በትኩረት አይመለከትም”[5]
አራተኛ ፡- አውድ
ሀውድ ማለት በጣም ልዩ የሆነ የነቢዩ ሰዐወ ተከታዮች የሚጠጡበት ወንዝ ሲሆን በሀዲስ እንደተብራራው ከወተት የነፃ፣ ከማር የበለጠ ጣዕም ያለው፣ከሚስክ በላይ ልዩ ሽታ ያለው አራቱም ማዕዘናት እኩል ሆኖ በጣም ሰፊ የሆነ ወንዝ ነው፡፡
በሀውድ ዙሪያ የተነገሩ ከሰላሳ በላይ የሆኑ ሰሃቦት ያስተላለፏቸወ በርካታ ሀዲሶች ተዘግበዋል፡፡ አነስ ኢብን ማሊክ እንዳስተላለፉት ነቢዩ ሰዐወ እንዲህ ብለዋል
« إن قدر حوضي كما بين أيلة إلى صنعاء من اليمن وإن فيه من الأباريق كعدد نجوم السماء »
“የሀውድ ስፋት ከአይላህ እስከ ሰንዳ ይደርሳል ኩባዮች ብዛት ደግሞ በከዋክብት ቁጥር ልክ ነው፡፡”[6]
አብደላህ ኢብን ዓምር ኢብኑል ዓስ እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል
« حوضي مسيرة شهر وزواياه سواء ماؤه أبيض من اللبن ، وريحه أطيب من المسك ، وكيزانه كنجوم السماء من يشرب منها فلا يظمأ أبدًا »
“የእኔ ሀውድ ርዝመት አንድ ወር የሚያስጉዝ ሲሆን ማዕዘናቱ እኩል ናቸው፡፡ ውሃም ከወተት የነፃ ጠረኑ ከሚስክ የሚበልጥ መጠጫዎቹ በከዋክብት ቁጥር ልክ ነው፡፡ ከሱ የጠጣ ለዘልአለም አይጠጣም፡፡”[7]
ሀውድ የሚገኘው በመሰብሰቢያ ሜዳ ላይ ሆኖ ከከውሰር ወንዝ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከውሰር ለነቢዩ የተሰጠ ጀነት ውስጥ የሚገኝ ወንዝ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል
{ إِنَّا أَعْطَيْنَاكَ الْكَوْثَرَ } (الكوثر : 1)
‹‹እኛ በጣም ብዙ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ፡፡›› ከውሰር 1
አምስተኛ፡- ሚዛን
የቂያማ እለት ከሚከሰቱና ሙስሊም ሊያምንባቸው ከሚገቡ ነገሮች ውስጥ የሰዎች ስራ የሚመዘንበት ሁለት ክንፍ ያለው እውነተኛ ሚዛን እንዳለ ማመን ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል
{ وَنَضَعُ الْمَوَازِينَ الْقِسْطَ لِيَوْمِ الْقِيَامَةِ فَلَا تُظْلَمُ نَفْسٌ شَيْئًا } . . الآية (الأنبياء : 47)
{ فَأَمَّا مَنْ ثَقُلَتْ مَوَازِينُهُ }{ فَهُوَ فِي عِيشَةٍ رَاضِيَةٍ }{ وَأَمَّا مَنْ خَفَّتْ مَوَازِينُهُ }{ فَأُمُّهُ هَاوِيَةٌ } (القَارعة : 6-9)
ቡኻሪና ሙስሊም ከአቡ ሑረይራ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ ሰዐወ እንዲህ ይላሉ
« كلمتان حبيبتان إلى الرحمن خفيفتان على اللسان ثقيلتان في الميزان سبحان الله وبحمده سبحان الله العظيم »
“ሁለት ቃላቶች ጌታ ዘንድ ተወዳጆች ለምላስ ቀላሎችና ሚዛን ላይ ክብደት አላቸው ሱብሃነሏህ ወቢሀምዲና (ምስጉኑ ጌታ ጥራት ይግባው) ሱብሃነሏሂል ዓዚም (ታላቁ ጌታ ጥራት ይግባው)”[8]
ኢብን መስዑድ በአስተላለፉት ሀዲስ “በአንድ ወቅት ኢብኑ መስዑድ ዛፍ ላይ ወጣና እግሮቹ ቀጨጭ ስለነበሩ ንፋስ ሲያወዛውዘው ያዩ ሰዎች ሳቁበት ነቢዩም ሰዐወ በምንድነው ምትስቁት? ሲሏቸው የአላህ መልዕክተኛ ሆይ በእግሮቹ ቅጥነት ነው የምንስቀው አሏቸው እሳቸውም ነፍሴ በእጁ ባለው ጌታ እምላለሁ ከኡሁድ ተራራ ይበልጥ ሚዛን ላይ ከባድ እግሮች ናቸው አሉ፡፡”
መረጃዎች እንደሚያመለክቱ በቂያማ እለት ሚዛን የሚመዝነው ሶስት ነገሮች ናቸው፡፡
- ስራዎች
ከላይ በተጠቀሰው የአቡሑረይራ ሀዲስ ነቢዩ ሰዐወ “ሁለት ቃላቶች … ሚዛን ላይ ከባዶች ናቸው፡፡” ብለዋል
- የስራ መዝገቦች
አቡደርዳህ ኢብን ዓምር ኢብኑል ዓስ በአስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ ሰዐወ እንዲህ ይላሉ “የቂያማ እለት አንደ ሰው የህዝቦች ፊት ይጠራ እያዳንዱ አይን የሚደርስበት ያህል ያላለቸው ዘጠና ዘጠኝ የኃጢአት መዝገቦቹ ይከፈታሉ ከዚያም ከነዚህ ኃጢአቶች የምትቃወመው አለን? ፀሐፊዎቼ በድለውሃልን? በመባል ሊጠየቅ “በፍፁም ጌታዬ” ይላል፡፡ በመቀጠል ይህን የፈፀምክበት በቂ ምክንያት ወይም ሌላ መልካም ተግባር አለህን? ሲባል ይፈራና የለኝም ጌታዬ ይላል አላህም እንዴታ እኛ ዘንድ የተቀመጠልህ አንድ መልካም ስራ አለኝ ዛሬ አትበደልም ይለውና ከአላህ ሌላ መመለክ የሚገባው እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ የሚል ፅሑፍ ያለበት ቁራጭ ወረቀት ይወጣና በአንዱ የሚዛን ሳህን ዘጠና ዘጠኝ መዝገቦች በሌላው የሚዛን ሳህን ሲቀመጡ ብጣሽ ወረቀቷ ክብደት ኖሯት መዝገቦችን ታመዝናለች ምክንያቱም ማንኛውም ነገር ከአላህ ስም ጋር ተመዝኖ ሊከብድ አይችልም፡፡”[9]
- ሰሪው ሰው እራሱ
የሚከተለው የቁርአን አንቀፅ ለዙህ ማስረጃ ይሆናል
{ فَلَا نُقِيمُ لَهُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ وَزْنًا } (الكهف : 105)
ስለኢብን መስዑድ እግሮች ሚዛን ላይ ከኡሁድ ተራራ የከበደ መሆን የተነገረው ሀዲስም ለዚህ ማስረጃው መረጃ ነው፡፡
[1] ቡኻሪ 3479
[2] ቡኻሪ 4935 ሙስሊም 2955
[3] ቡኻሪ 3414 ሙስሊም 2373
[4] ቡኻሪ 2412 ሙስሊም 2278
[5] ቡኻሪ 6527 ሙስሊም 2859
[6] ቡኻሪ 658ዐ ሙስሊም 23ዐ3
[7] ቡኻሪ 6579 ሙስሊም 2292
[8] ቡኻሪ 7563 ሙስሊም 2694
[9] ሙስነድ አህመድ 2/213 ቲርሚዚ 2639 ሙስተድረክ 529