በእለተ ትንሳኤ ሰዎች ከመቃብራቸው ወጥተው ከአሏህ ፊት ስለሚቆሙ፣ ይህ ማዕዘን «የቂያማ ቀን» ተብሎ ተጠርቷል፡፡ የመጨረሻ ቀን ተብሎም ይጠራል፡፡ አሁን ካለንበት (ከቅርቢቱ) አለም በኋላ ስለሚመጣም፣ የመቀስቀሻው ቀን («የውመል በእስ») ተብሎም ተጠርቷል – ሰዎች ከመቃብራቸው ስለሚነሱ፡፡ ይህ ቀን ብዙ ስያሜዎች አሉት -ከባድነቱንና ፍፁም አስጨናቂነቱን የሚያመላክቱ፡፡
የሰው ልጅ በህይወት ዘመንና ከሞት በኋላ የሚኖርባቸው አገሮች በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፤
o የዱንያ አገር (ስራ የምንሰራባትና የምንኖርባት አገር)
o ዳሩል በርዘኽ (የቀብር አገር)
o ዳሩል ቀራር (የመዘውተሪያ አገር)
«በመጨረሻው ቀን ማመን» ማለት፣ ቀኑ እንደሚከሰት ማመን ብቻ ሳይሆን ከወንጀል ተፀፅቶ በመመለስ ለዚያ ቀን የሚሆን መልካም ስራ በመስራት መዘጋጀት ማለት ነው፡፡ ሙስሊሞችን ከዚህ እጅግ በጣም ከባድ ከሆነ ቀን ቅጣትና ውርደት የሚያድናቸው መልካም ስራን መስራትና ከመጥፎ ስራዎች መራቅ እንዲሁም የሰሩት ወንጀል ካለ ተፀፅቶ ወደ አሏህ መመለስ ብቻ ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሒም እንዲህ ይላሉ፡-
«በሚቀሰቀሱበት ቀንም አታዋርደኝ፤ ገንዘብም ልጆችም በማይጠቅሙበት ቀን፣ ወደ አሏህ በንፁህ ልብ የመጣ ሰው ቢሆን እንጂ፡፡» (ሹዓራዕ፣ 87-89)
ቀኑ ታላቅና ከባድ ቀን ነው፡፡
«ሰው ከወንድሙ በሚሸሽበት ቀን፤ ከእናቱም፣ ከአባቱም፣ ከሚስቱም፣ ከልጁም፡፡» (አበሰ፣ 34-36)
«የመጨረሻ ቀን ወይም ሞቶ መቀስቀስ የሚባል ነገር የለም» የሚል ሰው ከከሀዲዎች ይቆጠራል፡፡ አሏህ እንዲህ ይላል፡-
«እነዚያ የካዱት በፍፁም የማይቀሰቀሱ መሆናቸውን አሰቡ፤ አይደለም፡፡ ‘በጌታዬ እምላለሁ፤ በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ፤ ከዚያም በሰራችሁት ሁሉ ትነገራላችሁ፤ ይህም በአሏህ ላይ ቀላል ነው’ በላቸው፡፡» (ተጋቡን፣ 7)
ሞቶ መቀስቀስን ለሚክዱ ሰዎች አሏህ በቁርዓኑ በቂ ምላሽ ሰጥቷቸዋል፤
«ሰማያትንና ምድርን መፍጠር ሰዎችን ከመፍጠር ይልቅ ታላቅ ነው፤ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም፡፡» (ጋፊር፣ 57)
አሏህ ሰዎችን ከሞቱ በኋላ የመቀስቀሱ ጉዳይ የማያጠራጥር መሆኑን ለማስረዳት፣ የሰው ልጅ የራሱን አፈጣጠር በውል እንዲመረምር ጋብዞታል፣ እንዲህ በማለት፡-
«እናንተ ሰዎች ሆይ! ከመቀስቀስ በመጠራጠር ውስጥ እንደ ሆናችሁ (አፈጣጠራችሁን ተመልከቱ)፤ እኛም ከአፈር ፈጠርናችሁ፤ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ፣ ከዚያም ከረጋ ደም፣ ከዚያም ከቁራጭ ስጋ… ፈጠርናችሁ፡፡» (ሀጅ፣ 5)
ሞቶ መቀስቀስ፣ ከዚያም በሰሩት መሰረት ዋጋ መሰጠት ባይኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሊረዳውና ሊገልፀው ከሚችለው በላይ እጅግ በረቀቀ ጥበብ የተሞላው የዚህ ፍጥረተ አለም መገኘት ወይም መፈጠር ቀልድ በሆነ ነበር፡፡ ግማሹ ሰው መልካም ሰርቶ፣ ለልፋቱ ቅንጣት ዋጋ ሳያገኝ፤ ከፊሉ ወንጀል ሰርቶ በጥፋቱ ምንም ሳይቀጣ ሁሉም አፈር ሆኖ ሊቀር? የግለሰቦችን ሀብትና ንብረት ከማውደምም አልፈው-ተርፈው፣ ክብር የተሰጠውን የሰውን ልጅ ህይወት አላግባብ የቀጠፉና የሰው ልጅ ደም እንደ ጎርፍ እንዲፈስ ያደረጉ ሁሉ ተገቢ ዋጋቸውን ሳያገኙ አፈር ለብሰውና በስብሰው ሊቀሩ? ይህ ከአሏህ ፍትሀዊነትና ጥበበኛነት ጋር ፍፁም የሚሄድ አይደለም፡፡ አሏህ እንዲህ ይላል፡-
«የፈጠርናችሁ ለከንቱ መሆኑን፣ እናንተም ወደ እኛ የማትመለሱ መሆናችሁን ጠረጠራችሁን?» (ሙዕሚኑን፣ 115)
አሏህ ከሀዲዎችንና ሙሽሪኮችን በመጨረሻ ወደ እርሱ እንደሚመለሱና ሂሳብ እንደሚደረጉ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያመላክተው ሞቶ መቀስቀስ አይቀሬ መሆኑን ነው፡: ይህች ያለንባት አለም የስራ አገር ስትሆን፣ የመጨረሻዋ አለም ደግሞ ዋጋ የሚሰጥባት አገር ናት፡፡ ይህ የአሏህ ጥበብ ነው፡፡
የትንሳኤ ቀን ከሞት በኋላ ያለውን ሁሉ ያካትታል፡፡ ሰዎች ሩሀቸው (ነፍሳቸው) ከወጣችበት ሰዓት ጀምሮ ከዚህች ምድራዊ አለም ወጥተው ወደ መጨረሻው አለም ይገባሉ፡፡ የትንሳኤ የመጀመሪያው ምዕራፍ «ሀ» የሚለው፣ የሟች ነፍስ ከአካሉ እንደ ተለየች ነው፡፡ በሀዲስ እንደ ተዘገበው፣ አንድ ሰው ሞቶ ቀባሪዎች አፈር መልሰው ዘወር እንዳሉ የቀባሪዎችን የጫማ ኮቴ ያዳምጣል፤ ሩሁም (ነፍሱ) ወደ አካሉ ትመለሳለች፡፡ ሁለት መላኢካዎች ሟቹን በማስቀመጥ፣ «ጌታህ ማን ነው? ሀይማኖትህ ምንድን ነው? ነብይህ ማን ነው?» የሚሉ ሶስት ጥያቄዎችን ይጠይቁታል፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል – «መላኢካዎች፣ እኛ ሳናያቸው እንዴት ወደ መቃብሩ ሊመጡ ይችላሉ?» የሚል፡፡ ይህን ጥያቄ በጥያቄ መመለስ ይቻላል፤ «ሞቶ ወደ ተቀበረ ሰው ዘንድ የሚመጡ መላኢካዎችን ይቅርና በአካልህ ውስጥ አብራህ ያለችውን፣ ለህልውናህ መሰረት የሆነችውንና ስትለይህ በድን የምታደርግህን ነፍስህን አይታሀት ታውቃለህን?» አዎ – ማንም ቢሆን ነፍሱን አይቷት አያውቅም፡፡ ስለሆነም አለማየታችን የአንድን ነገር አለመኖር ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ከነፍሳችን ጀምሮ፣ ከእኛ የተሰወሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሌላው ይቅርና ለሰው ልጅ በህልውና ለመኖር ከሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ፣ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው አየር ነው፡፡ አየር ያጣ ሰው፣ በትንሽ ደቂቃ ውስጥ ህይወቱ ያልፋል፡፡ አየር ለሰው ልጅ ይህን ያህል ቅርብና ከምንም በላይ የሚያስፈልገው ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ግን አየር ጥቁር ይሁን፣ ቀይ አይቶት አያውቅም፡፡ የሰው ልጅ አናቱን የተሸከመለትን አንገቱን ይቅርና ለሁለቱ አይኖቹ እጅግ በጣም ቅርብ የሆነውን የሰውነቱን አካል (አፍንጫውን) አሟልቶ ማየት አይችልም፡፡ የሰው ልጅ ይህን ያህል ደካማ ፍጡር ነው፡፡ ስለዚህ የማናያቸውን መላኢካዎች በመላክ ሟቹን እንዲጠይቁ ማድረግ፣ ፍጹም የሆነ ጥበብና ችሎታ ባለቤት ለሆነው ለአሏህ እጅግ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሙዕሚኖች ከሆን ደረታችንን ለአሏህ ህግ ክፍት በማድረግ አምነን መቀበል ብቻ ነው፡፡
ሟቹ ቀደም ሲል የቀረቡትን የቀብር ውስጥ ጥያቄዎች በትክክል ከመለሰ ፈተናውን ያልፋል፤ የተመቻቸ የቀብር ኑሮም ይኖራል፡፡ መልሱ ካልተሳካለትም ይከስራል፡፡ ሟቹ ሙዕሚን ከሆነ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ያለምንም ጥርጥር ተስማሚ መልስ ይሰጣል፡፡ «ጌታዬ አሏህ ነው፡፡ እምነቴ እስልምና ነው፡፡ ነብዩ ሙሀመድ መልዕክተኛዬ ነው» ይላል፡፡ ከዚያም ተጣሪ ይጣራል፤ ‹‹ባሪያዬ እውነት ተናገረ፡፡ ከጀነት ምንጣፍ አንጥፉለት፤ መቃብሩን የአይን እርቀት ያህል አስፉለት፤ ወደ ጀነት በርን ክፈቱለት›› ይባላል፡፡ የጀነት ሽታዋ ይመጣለታል፤ በጣፋጭ ሽታዋም ይታወዳል፡፡ የጀነት ደረጃውንም ይመለከታል፡፡ ሟቹም ‹‹ጌታዬ ሆይ! ወደ ቤተሰቦቼ (የጀነት ባልደረቦቼ) እና ወደ ገንዘቤ (የሰራሁት መልካም ሰራ) እመለስ ዘንድ ቂያማን አቁመው›› ይላል፡፡ ቀብሩም ከጀነት ጨፌዎች፣ አንዱ ጨፌ ይሆንለታል፡፡ የሰው ልጅ የቀብርን ኬላ ካለፈ፣ ከዚያ በኋላ ያለው በጣም ቀላል ነው የሚሆነው፡፡
በዚህ ተቃራኒ ደግሞ ሟቹ ሙናፊቅ ከሆነና በጥርጣሬ ህይወት ሲኖር ከነበረ፣ ሁለቱ መላኢካዎች ከፍ ሲል የተገለፁትን ሶስት ጥያቄዎች ሲያቀርቡለት ምላሹ፣ «አላውቅም፤ ሰዎች የሆነ ነገር ሲናገሩ ሰምቼ ተናግሪያለሁ እንጂ፣ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም›› ይላል፡፡ ይህን የሚልበት ምክንያትም ይህ ሰው በዚህች ምድራዊ ህይወት ሲኖር በልቡ እምነት ስላልነበረው ነው፡፡ «የሆነ ነገር ሲናገሩ ሰምቼ ተናግሬያለሁ» የሚል ምላሽ መስጠቱ፣ ሙስሊሞችን መስሎ ሙሰሊሞች የሚናገሩትን ቋንቋ ሲናገርና የሚተገብሩትን ሲፈጽም የነበረ ሙናፊቅ ሰው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሟቹ ትክክለኛ እምነት እስከ ሌለው ድረስ፣ ቋንቋ አጣርቶ የሚችል ቢሆንም ቀብር ውስጥ ግን ትክክለኛውን መልስ መስጠት የማይችል መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ጥያቄው የቋንቋ ችሎታ መኖር አለመኖር ወይም ቋንቋን አቀላጥፎ የመናገር ወይም ያለመናገር ጉዳይ አይደለም፤ በእምነት ላይ ጸንቶ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንጂ፡፡ ሙናፊቁ ቀብሩ ውስጥ ተገቢውን መልስ መስጠት ሳይችል ሲቀር፣ ልክ እንደ ሙዕሚኑ ተጣሪ ይጣራል፤ «ባሪያዬ ዋሸ፡፡ ከእሳት የሆነ ምንጣፍ አንጥፉለት፤ ወደ እሳት በርን ክፈቱለት፡፡» የጀሀነም መጥፎ ሽታዋና መርዟ ይላክለታል፡፡ የቀኝና የግራ ጎን አጥንቶቹ እርስ በርሳቻው እስኪሰካኩ ድረስ የተኛበት ቀብር ይጠብበታል፤ እናም ከእሳት ጉድጓዶች አንዱ ጉድጓድ ይሆንበታል፡፡ ሟቹም «የቂያማን (የትንሳኤን) ሰዓት አታቁመው» ይላል፤ ምክንያቱም ከትንሳኤ በኋላ የሚገጥመውን ከዚህ የከፋ ቅጣት ስለሚያውቀው፡፡
ሙእሚኖችና ሙናፊቆች በቀብር ውስጥ የሚያጋጥማቸውን የተለያየ ሁኔታ በተመለከተ አሏህ እንዲህ ይላል
«አሏህ እነዚያን ያመኑትን፣ በቅርቢቱም ህይወት በመጨረሻይቱም (በመቃብር) በተረጋገጠ ቃል ላይ ያደርጋቸዋል፤ ከሀዲዎችንም አሏህ ያሳስታቸዋል፤ አሏህም የሚሻውን ይሰራል፡፡» (ኢብራሂም፣ 27)