ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ነው:: የአላህ ሰላም እና እዝነት የመልዕክተኞች ሁሉ መደምደሚያ በሆኑት ነብይ በሙሀመድ በቤተሰቦቻቸው እና በባልደረቦቻቸው ላይ ይሁን:: ኢስላም ማለት ከአላህ በቀር በሀቅ የሚመለክ አምላክ የለም ሙሀመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ) የአላህ መልዕክተኛ ናቸው::ብሎ በልቦና ማመን፣ በአንደበት መመስከር እና በተግባርም ማረጋገጥ ሲሆን፤ በስድስቱ የእምነት መሰረቶች ማመን እና አምስቱን የኢስላም መሰረቶች መተግበር፣ እንዲሁም ይሄንኑ ተግባር ባማረ መልኩ ማከናወን (ኢህሳንን) ያጠቃልላል::
ኢስላም፤ አላህ የነብያትንና የመልዕክተኞች (ሩስሎች) መደምደሚያ በሆኑት ሙሀመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ላይ ያወረደው የመልዕክቶቹ ሁሉ መቋጫ ነው:: አላህ ዘንድም ከኢስላም በቀር ተቀባይነት ያለው ሀይማኖት የለም:: ይህንን እውነተኛ ሀይማኖት አላህ ገር እና ቀላል፣ አዳጋችም ሆነ አስቸጋሪ ነገር የሌለበት አድርጎታል:: አማኞችን ከአቅም በላይ የሆነ ትዕዛዝ አላዘዛቸውም፣ የማይችሉትንም ግዴታ አላደረገባቸውም:: ኢስላም፤ መሰረቱ የአላህ አንድነት (ተውሂድ)፣ መነሻው ሀቅና እዝነት፣ መለያው እውነተኝነት፣ መሽከርከሪያ ዛቢያው ፍትህ ነው:: ኢስላም ሰዎችን ለመንፈሳዊ ህይወታቸውም ሆነ ለዓለማዊ ኑሮቸው ጠቃሚ ወደ ሆነ ነገር ሁሉ የሚመራ፣ በአንጻሩም ጎጂ ከሆነ ነገር ሁሉ የሚያስጠነቅቅ ሀይማኖት ነው::
ኢስላም፤ አላህ የሰው ልጆችን እምነት እና ባህሪ ያስተካከለበት፣ የዱንያን እና የአኼራ ህይወት ያሳመረበት፣ የተራራቁ አመለካከቶችን እና የተለያዩ ዝንባሌዎችን አንድ በማድረግ ከንቱ ከሆነ ጽልመት አጥርቶ ወደ እውነት የመራበት ሀይማኖት ነው:: አጠቃላይ ህግጋቱም ሆነ መልዕክቶቹ ፍጹም በሆነ መልኩ ተብራርተዋል:: ኢስላም ሀቅን እንጂ አልተናገረም ! በእውነት እና በፍትህ እንጂ አልፈረደም ! ትክክለኛ እምነትን እና ቀና የሆኑ ተግባራትን አስተምሮል፣ በእውነት ኢስላምን የሚኖር ሰው ግሩም ባህሪን እና የላቀ ስርዓትን ይላበሳል::
የኢስላም መልዕክት የሚከተሉትን አላማዎች ያካትታል፦
1_ የመጀመሪያ ዓላማው የሰው ልጆችን ከፈጣሪያቸው ጋር ማስተዋወቅ ሲሆን፤ ያማሩ ስሞቹ ወደር እንደሌላቸው፣ መልካም ባህርያቱ ምሳሌ እንደሌላቸው፣ በጥበብ የተሞሉ ስራዎቹንም ማንም እንደማይጋራው፣ እንዲሁም በፍፁም ቢጤ እንደሌለው አምልኮም ለእርሱ ብቻ እንደሚገባ ያስተምራል::
2_ የሰው ልጆች አላህ የደነገጋቸውን እና በዱንያም ሆነ በአኼራ ስኬታማ የሚያደርጋቸውን ትዕዛዛቱን በመፈፀም፣ ከከለከላቸውም ነገሮች በመቆጠብ፣ አጋር የሌለውን አላህን ብቻ እንዲያመልኩ ይጣራል::
3_ የሰው ልጆች ከሞት በኌላ የሚኖራቸውን ዕጣ ፈንታ፣ ከሞት በኌላ እስከ ሚቀሰቀሱ እና በትንሳኤ ቀን የሚያጋጥማቸውን ክስተት ያስተምራል:: አላህም ባሮቹን በመጪው አለም እንደሚተሳሰባቸው ይናገራል:: የመልካም ስራ ዋጋ መልካም፣ የክፉ ስራ ምንዳም ክፉ በመሆኑ እንደየስራቸው መጨረሻቸው ጀነት ወይም እሳት እንደሚሆን ያስገነዝባቸዋል::
ከዚህ በመቀጠል ዋና ዋናዎቹን የኢስላም መርሆዎች አጠር ባለ መልኩ ለማብራራት እንሞክራለን፦
አርካኑል ኢማን (የዕምነት ማዕዘናት)
1_ በአላህ ማመን፤ በአላህ ማመን የሚከተሉትን ነጥቦች ያካትታል፦
- በአላህ ጌትነት ማመን፦ አላህ የነገሮች ሁሉ ባለቤት፣ የፍጡራንን እንቅስቃሴዎች በሙሉ የሚያስተናብር በእነርሱም ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው ፈጣሪ ጌታ እንደሆነ ማመን ነው::
- በአላህ ብቸኛ ተመላኪነት ማመን፦ አላህ ዕውናተኛ አምላክ እንደሆነና ከርሱ ሌላ የሚመለክ ማንኛውም አካል ከንቱ እንደሆነ ማመን ነው::
- በአላህ ስሞችና ባህሪያት ማመን፦ በቁርአንና በሀዲስ በተገለፀው መሰረት አላህ የላቁ ምሉዕ የሆኑ ባህሪያት እና መልካም ስሞች እንዳሉት ማመን ነው::
2_ በመላዕክት ማመን፤ መላዕክት አላህ የፈጠራቸው ፍጡራኖች፣ ዘወትር እርሱን የሚገዙ፣ ለትዕዛዞቹም ተገዢ የሆኑ የተከበሩ ባሮቹ ናቸው:: አላህ የለያየ የስራ ድርሻ ሰጥቷቸዋል:: ከእነርሱ መካከል ጅብሪል የተባለው የወህይ (ከአላህ ወደ ነብያት የሚተላለፍ መልዕክት) ወኪል ሲሆን ከነብያትና ከሩሱሎች አላህ ወደሻው የወህይን መልዕክት ይዞ ይወርዳል:: ሚካል (ሚካኢል) የተባለው መልዐክ ደግሞ ለዝናብና ለተክሎች የተመደበ ነው:: ኢስራፊል በዓለም ጥፋትና በትንሳኤ ቀን በቀንድ ለመንፋት ተመድቧል:: እንዲሁም መለኩልመውት የተባለው መልዐክ በሞት ጊዜ ነፍስን ከስጋ ለመለየት ተመድቧል::
3_ በመፅሐፍት ማመን፤ አላህ በመልዕክተኞቹ ላይ እውነተኛ ፀጋን ቅን መመሪያንና ተሀድሶን ያዘሉ መፅሐፍትን አውርዷል:: ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉትን እናውቃለን::
ተውራት፦ አላህ በነብዩ ሙሳ (ዓለይሂ ሰላም) ላይ ያወረደው ሲሆን ለኢስራኤል ልጆች ከተሰጡት ታላላቅ መፅሐፍት አንዱ ነው::
ኢንጂል፦ አላህ በነብዩ ዒሳ (ዓለይሂ ሰላም) ላይ ያወረደው መፅሐፍ ነው::
ዘቡር፦ አላህ በነብዩ ዳውድ (ዓለይሂ ሰላም) ላይ ያወረደው መፅሐፍ ነው::
ሱሑፍ፦ አላህ በነብዩ ኢብራሂም (ዓለይሂ ሰላም) ላይ ያወረደው መፅሐፍ ነው::
ታላቁ ቁርኣን፦ አላህ በመጨረሻው ነብይ በሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ላይ ያወረደው መፅሐፍ ሲሆን፤ እስከ ዕለተ-ትንሳኤ በፍጡራን ሁሉ ላይ ማስረጃ ሆኖ ስለሚኖር ከቁርኣን በፊት የነበሩ መፅሐፍትን በሙሉ አላህ በእርሱ ሽሯቸዋል:: የጥበቃውንም ዋስትና አላህ እራሱ ወስዷል::
4_ በሩሱሎች (በመልዕክተኞች) ማመን፦ አላህ ወደ ፍጡራን መልዕክተኞችን ልኳል:: የመጀመሪያው ኑህ (ዓለይሂ ሰላም) ሲሆኑ የመጨረሻው ደግሞ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ናቸው:: የመርየም ልጅ ዒሳንና ዑዘይርን ጨምሮ ሁሉም(የአላህ ሰላት እና ሰላት በነርሱ ላይ ይሁን) ከሰው ልጅ የሆኑ ፍጡራን ናቸው:: የአላህን ብቸኛ ጌትነት(አምላክነት) እንዲጋሩ የሚያደርጋቸው ምንም ዓይነት መለኮታዊ ባህሪ የላቸውም:: አላህ ከባሮቹ መካከል መልዕክት አድራሾች በማድረግ አክብሯቸዋል:: አላህም መልዕክቱን በሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ላይ በወረደው ዘልዓለማዊ ኪዳን ደምድሟል:: አላህ ለሰው ዘር በሙሉ ልኳቸዋል:: ከእርሳቸውም በኋላ ነብይ የለም::
5_ በመጨረሻው ቀን ማመን፦ የመጨረሻው ቀን አላህ ፍጥረታትን በሙሉ የሚሰበስብበት፣ የሰው ልጆችን ታላቅ ተድላ ወይም አሳማሚ ቅጣት ባለበት ዓለም እንዲኖሩ የሚያደርግበት፣ ከመቃብራቸው ህያው አድርጎ የሚያስነሳበት ቀን ነው:: በመጨረሻው ቀን ማመን ከሞት በኋላ ባሉ ክስተቶች ሁሉ ማመንን ያካትታል:: ይህም በቀብር ፈተና፣ በውስጡ ባለው ጸጋና ቅጣት ከዚያም በትንሳኤ፣ መሰብሰብና መመርመር እንዲሁም ጀነትና ጀሀነም ውስጥ ባለው ሁሉ ማመንን ያጠቃልላል::
6_በቀደር(በውሳኔ) ማመን፦ በቀደር ማመን ማለት አላህ ቀድሞ ባወቀውና ጥበቡ በፈረደው መሰረት ክስተቶችን እንደወሰነ በዚሁም መሰረት ፍጡራንን እንዳስገኘ ማመን ነው:: አላህ ዘንድ ሁሉም ነገር ጥንቱኑ(በአዘል) የታወቀ ነው:: በተጠበቀው ሰሌዳ(ለውሀል መህፉዝ) የሰፈረ ነው:: አላህ ሁሉንም በፍላጎቱ ፈጥሯል:: ከአላህ ፍላጎት(መሺዓ)፣ ክዋኔና መፍጠር በቀር የሚከሰት ነገር የለም::
አርካኑል ኢስላም(የኢስላም ማዕዘናት)
ኢስላም በአምስት መሰረቶች ላይ የተገነባ ነው:: ማንኛውም ሰው ትክክለኛ ሙስሊም ሊሆን የሚችለው በእነዚህ አምስት መሰረቶች አምኖ ተግባራዊ ሲያደርጋቸው ብቻ ነው:: እነርሱም፦
1_ «ላ ኢላሀ ኢልለላህ ሙሐመዱን ረሱሉላህ» ከአላህ በቀር በሀቅ የሚመለክ አምላክ የለም፣ ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ ናቸው ብሎ መመስከር ነው:: ይህች ምስክርነት ወደ ኢስላም መግቢያ ቁልፍ ናት:: ኢስላምም የሚጋነባው እርሷን መሰረት አድርጎ ነው:: «ኢላህ» ማለት «ማዕቡድ» ወይም የሚመለክ ማለት ነው:: እውነተኛው አምላክ አላህ ብቻ ነው:: ከእርሱ በቀር የሚመለኩ ሁሉ ከንቱ አማልክት ናቸው::
በነብዩ ሙሀመድ(r) መልዕክተኝነት ማመን ማለት ደግሞ ነብዩ(r) የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል፣ ያዘዙትን መታዘዝ፣ ያወገዙትንና የከለከሉትን መከልከል እንዲሁም አላህን እርሳቸው በደነገጉት የአምልኮ ስርአት መሰረት ብቻ ማምለክ ማለት ነው።
2_ ሰላት፦ በቀንና በማታ አምስት ጊዜ የሚፈፀሙ ሰላቶች(ስግደቶች) ናቸው:: ሰዎች አላህ ባባሮቹ ላይ ያለውን ሀቅ እንዲወጡ፣ ለፀጋዎቹም ምስጋና እንዲያደርሱ፣ ከአፀያፊና ከተጠላ ተግባር ሁሉ እንዲርቁ ሰላትን ደነግጎላቸዋል:: ሰላት በትክክል ከተከወነ በአላህ ፍቃድ ከዝሙትና ከፀያፍ ተግባር ሁሉ ይጠብቃል:: በአንድ ሙስሊምና በጌታው መካከል አገናኝ ስለሆነም ሙስሊሙ በሰላቱ ውስጥ ጌታውን ይማፀናል:: በሚስጥርም ወደርሱ ይፀልያል::
አላህ፤ የኢማን ጥንካሬና ፅድቅ እንዲሁም በዚህ አለምም ሆነ በመጪው አለም የሚገኝ መልካም ምንዳ ሰላትን ተከትሎ እንዲመጣ አድርጎል:: እንዲሁም ታላቅ አካላዊና መንፈሳዊ እርካታን ይሰጣል:: በዱንያም ሆነ በአኺራ ስኬታማ ያደርጋል::
3_ ዘካ፦ ዘካ ማለት፤ ግዴታ የሆነበት ሰው በየአመቱ ለሚገባቸው ችግረኞችና ለሌሎች ዘካ እንዲወስዱ ለተፈቀደላቸው ሰዎች የሚከፍለው የግዴታ ምፅዋት ነው::አንድ ሰው ገንዘቡ የዘካ ኒሷብ (ዘካ ግዴታ የሚሆንበት አነስተኛው የገንዘብ መጠን) ላይ እስካልደረሰ ድረስ ዘካ ግዴታ አይሆንበትም:: ግዴታ የሚሆነው በባለሀብቶች ላይ ሲሆን ይህም ሀይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡና ኢስላማዊ ባህሪ በውስጣቸው እንዲያብብ ነው:: ዘካን መክፈል ወንጀልን ያስምራል:: በአንድ ሙስሊምና በንብረቱ ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ ጥፋቶች አላህ ይጠብቀው ዘንድ ምክንያት ይሆናል። ለችግረኞችና ዕርዳታ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ፣ ብሎም ለማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ ነው:: ከመሆኑም ጋር ለባለሀብቶች አላህ ከሰጣቸው ገንዘብና ንብረት ውስጥ መክፈል የሚገባቸው የዘካ መጠን በጣም ጥቂት ነው::
4_ ፆም፦ ፆም ማለት በየአመቱ እንደ ጨረቃ አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር የተከበረውን ወርሃ ረመዳን መፆም ነው:: በረመዳን በየቀኑ ጎህ ከቀደደበት ሰዓት ጀምሮ ጀምበር እስክትጠልቅ ድረስ በኢስላም ከተወሰኑ መሰረታዊ ፍላጎቶች(ከምግብና ከማጠጥ እንዲሁም ከስጋዊ ተራክቦ) በመቆጠብ የዓለም ሙስሊሞች በሙሉ በአንድ አይነት ሁኔታ ይፆሙታል:: አላህም በዚህ መልካም ተግባራቸው ከችሮታው በጎን በመዋል፣ ዕምነታቸውን በመሙላትና ወንጀላቸውን በመማር ይከሳቸዋል:: እርሱ ዘንድ ያላቸውን ደረጃ ከፍ ያደርግላቸዋል:: እንዲሁም አላህ ለፆመኞች ካዘጋጀው የዱንያና የአኺራ መልካም ነገሮች ሁሉ ይቸራቸዋል::
5_ ሐጅ፦ ሐጅ ማለት ወደ ተከበረው የአላህ ቤት(ካዕባ) ለየት ያለ ዒባዳ (አምልኮ) ለመፈፀም በተወሰነ የጊዜ ቀመር የሚደረግ ጉዞ ነው:: ሐጅ በኢስላም ታላቅ ቦታ ያለው አምልኮ ነው:: አቅም ባለው ማንኛውም ሙስሊም ላይ በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ አላህ ግዴታ አድርጎታል:: ለሐጅ ስነስርዓት ሙስሊሞች ከመላው ዓለም በምድር ላይ ተመራጭና ቅዱስ በሆነው ስፍራ ይሰባሰባሉ:: አንድ ዓይነት ልብስ በመልበስ አንዱን አምላካቸውን ያመልካሉ:: በመሪና በሚያስተዳድራቸው ሰዎች፣ በሀብታምና በድሀ፣ በነጭና በጥቁር መካከል ልዩነት ሳይኖር በጊዜና በቦታ የተወሰኑ የሐጅ አምልኮ ተግባሮችን በአንድነት ያከናውናሉ:: ከዋና ዋናዎቹ የሐጅ ተግባራት መካከል በዓረፋ መቆም፣ በተከበረው ካዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ማድረግ እና ሰፋና መርዋ በተባሉት ተራራዎች መካከል መመላለስ ይገኙበታል:: ሐጅ ለመቁጠርና ለመዘርዘር የሚያዳግቱ እጅግ ብዙ ሀይማኖታዊና ማህበራዊ ጥቅሞች አሉት::
አል-ኢህሳን
ኢህሳን ማለት በልቦናና በተግባር አላህን እንደምታየው አድርገህ ማምለክ ነው:: አንተ ባታየው እርሱ ያይሀልና! ይህንን በልቦና በማሳደር በነብዩ(ሰለላሁ ዐለይሂወሰለም) ሱና(ፈለግ) መሰረት ዒባዳን መከወን ፈለጋቸውንም አለመፃረር ኢህሳን ነው::
ከዚህ በላይ ስለ ኢስላምና ስለ ኢማን መሰረቶች እንዲሁም ስለ ኢህሳን የሰፈረውን አጠር ያለ ማብራሪያ «ኢስላም» የሚለው መጠሪያ ያካትተዋል::
የመጨረሻው ክፍል እንደሚከተለው ይቀርባል
….
እንደሚታወቀው ኢስላም የግለሰቦችንም ሆነ የኢስላማዊ ማህበረሰቦችን ሕይወት በዱኒያም ሆነ በአኺራ ለስኬት በሚያበቃቸው መልኩ ስርዓት አስይዟል:: ለምሳሌ፦ ትዳርን ፈቀደ አበረታታም! በአንፃሩም ዝሙትንና ግብረ-ሰዶማዊነትን እንዲሁም መሰል ፀያፍ ተግባራትን ከለከለ:: ዝምድናን መቀጠልን፣ለፍጡራን ማዘንን፣ ድሆችንና ችግረኞችን መንከባከብን ግዴታ አደረገ:: መልካም ፀባይን ሁሉ አስተማረ:: ከመጥፎ ፀባይም ሁሉ አስጠነቀቀ:: ለተከታዮቹ ከንግድ፣ ከኪራይና ከመሳሰሉት የገቢ ምንጮች የሚገኝን ሀላል ትርፍ ፈቀደ:: አራጣን እና ሊሎችን ማጭበርበር ያለባቸውን የንግድ እንቅስቃሴዎች በሙሉ እርም አደረገ::
ሰዎች ለህግጋቱ ከመገዛትና የሌሎችን መብት ከመጠበቅ አኳያ ስለሚለያዩ ዝሙት፣ አስካሪ መጠጥ መጠጣትና በመሳሰሉት የአላህን ሕግ በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ቅጣትን ደንግጎል:: እንዲሁም በሰዎች ደም፣ ንብረትና ክብር ላይ በሚፈፀሙ እንደ ግድያ፣ ስርቆት፣ ስም ማጥፋት፣ የሰዎችን ንብረት ያለአግባብ መውሰድ የመሳሰሉት ወንጀሎችም ላይ ገሳጭ ቅጣቶችን ደንግጓል:: ቅጣቶቹ በደል የሌለባቸው ፍጹም ፍትሀዊ ናቸው::
ኢስላም በገዢና በተገዢ መካከል ያለውን ግንኙነት በመወሰን አስተዳደርን ስርዓት አስይዟል:: በኢስላማዊ ስርዓት ማህበረሰቡ ወንጀልነክ ባልሆኑ ነገሮች ሁሉ ለገዢው መደብ ታዛዥ እንዲሆን ግዴታ አድርጎል:: በግለሰቦችና ባጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ በሚያስከትለው መዘዝ ሳቢያ በመሪዎች ላይ የሚደረግ አመጽን ከልክሏል::
በመጨረሻም ይህችን አጠር ያለች መልዕክት በዚህ ማጠቃለያ ሀሳብ እንቌጫለን::
ኢስላም መልካም ባህሪንና ጥሩ ማህበራዊ ግንኙነትን ለተከታዮቹ አስተምሮል:: በሰው ልጆችና በጌታቸው፣ በግለሰቦችና በሚኖሩበት ማህበረሰብ መካከል በሁሉም መስክ ትክክለኛና መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ያስችላል:: በአንጻሩም መጥፎ ከሆኑ ባህሪያትና ለመልካም ግንኙነት መሻከር ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ሁሉ አስጠንቅቌል:: ይህም የኢስላምን ሙሉዕነትና በሁሉም ጎኑ ለሰው ልጆች የሚበጅ እንደሆነ በጉልህ የሚያሳይ ነው::
ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ነው::