የቃለ ተውሂድ ምስክርነት፤ “አሽሀዱ አን ላ ኢላሀ ኢለላህ” ‹‹ከአላህ በስተቀር በሀቅ አምልኮ የሚገባው እንደሌለ እመሰክራለሁ» ማለት ሲሆን “ወአሽሀዱ አነ ሙሀመደን ረሱሉላህ” የሚለው ደግሞ «ሙሀመድ عየአላህ መልዕክተኛ መሆናቸዉን እመሰክራለሁ» ማለት ነው፡፡ አነዚህን ሁለት የምስክርነት ቃላት ማንኛዉም ሙስሊም ጥቅል በሆነ መልኩ ሊያዉቃቸዉ እና ሊመሰክርባቸው ይገባል፡፡ እንደሚታወቀዉ፤ ምስክርነት በእዉቀት ላይ የተመሰረተ መሆኑ የግድ ነዉ፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡-
﴿فَاعْلَمْ أَنَّهُ لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ وَاسْتَغْفِرْ لِذَنْبِكَ وَلِلْمُؤْمِنِينَ وَالْمُؤْمِنَاتِ﴾ محمد 19
“እነሆ! ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩን እወቅ፤ ስለ ስህተትህም ለምዕመናንም ምህረትን ለምን…” ሙሐመድ 19
“ላ ኢላሀ” የሚለው የአረፍተ ነገሩ ክፍል ከአላህ ውጪ የሚመለኩ አማልክትን በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ «ማፍረስ ወይም ነፍይ» ሲሆን “ኢለላህ” የሚለው የአረፍተ ነገሩ ክፍል ደግሞ አምልኮ ለአንድ አላህ ብቻ መሆኑንና ምንም አጋር እንደሌለው የሚያረጋግጥ «ማጽደቅ ወይም ኢስባት» ነው።
አላህ አንዲህ ይላል፡-
﴿فَمَنْ يَكْفُرْ بِالطَّاغُوتِ وَيُؤْمِنْ بِاللَّهِ فَقَدِ اسْتَمْسَكَ بِالْعُرْوَةِ الْوُثْقَى لَا انْفِصَامَ لَهَا﴾ البقرة 256
“በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ ” አል-በቀራህ 256
‹ሙሀመደን ረሱሉላህ› የሚለው የምስክርነት ቃል መልዕክት ደግሞ ሙሐመድع ወደ ሰው ልጆች ሁሉ የተላኩ የአላህ ባሪያ እና መልዕክተኛ መሆናቸውን ማመንና ማረጋገጥ ነው፡፡ ነብዩ ع የተናገሩትን ማመን፣ ያዘዙትን መተግበር፣ የከለከሉትን መራቅ እና አላህን በእሳቸዉ ፈለግ መሰረት ማምለክን ግዴታ ያደርጋል፡፡