አህሉሱና የአላህን ባህርያት ሲያፀድቁ

0
66

አህሉሱና የአላህን ባህርያት ሲያፀድቁ ያለ “ተክይፍ” እና ያለ “ተምሢል” ومن غير تَكْييفٍ وَلا تَمْثِيل

አህሉሱና የአላህን ባህርያት ሲያፀድቁ ከማመሳሰልና የባህሪውን ሁኔታ ከመናገር ይርቃሉ። ይህ ደግሞ የአህሉሱናን ዓቂዳ የአላህን ባህሪዎች ከፍጡራን ባህሪዎች ጋር ከሚያመሳስሉት ሙሸቢሀዎች (ሙመሲላዎች) አቂዳ ይለያል።

“ተክዪፍ” (የባህሪዉን ሁኔታና ምንነት መናገር)፦

 የባህሪውን ሁኔታና ምንነት መወሰን እና እንዲህ ነው እንዲያ ነው የሚል ግምት መስጠት ሲሆን፤ አንድ ሰው ለአላህ አምሳያ ባያደርግለትም “እንዲህ አይነት ነው” የሚለውን ምስል እና ሁኔታ በአዕምሮው ከቀረጸ ተክዪፍ በተባለው የጥመት በር ከቀጥተኛው መንገድ አፈንግጧል ይባላል።

 ለምሳሌ፦ ሂሻምያ የተባለው አንጃ መስራች የሆንነው ሂሻም ኢብኑል ሀከም ስለ አላህ ዛት ሲናገር የአካሉ “እርዝመት እና ጎኑ አይለያይም” በሚል ይገልጻል። ‘እንደ’ የሚለዉን ማመሳሰያ ቃል ባይጠቀምም ለአላህ የራሱን ግምት በመስጠት ተክዪፍ ፈጽሟል። በዚህ መልኩ ከይፊያን መዘርዘር ፈጽሞ የስህተት ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ከአላህ በቀር የእርሱን ባህሪዎች ሁኔታ የሚያውቅ የለም፤ ፍጡራን ይህን ማወቅ አይችሉም፡፡ እንደሚታወቀው፤ የአንድ ነገር ከይፊያ እና ምንነት የሚታወቀው፤ ከተከታዮቹ መንገዶች አንዱን በመጠቀም ነው።

  • እርሱን በማየት
  • አምሳያውን በማየት፤
  • ምንነቱን በተመለከተ እውነተኛ የሆነ ገለጻ በማግኘት

 አላህን አላየነዉም፣ አምሳያም የለዉም፣ አላህ እራሱን የገለፀባቸዉን ስሞችና ባህሪዎች ትርጓሜ እንረዳለን። ይሁንና ስለ “ከይፊያ” ወይም “የባህሪያቱን ሁኔታ ምንነት” አልነገረንም፤ ስለዚህ የባህሪያቱን ከይፊያ ሁኔታ ልናውቅ አንችልም። ጌታችን አላህ የላቀና የተቀደሰ ነው፡፡

 ሰለፎች “ካለ ተክዪፍ” ብለው ሲናገሩ፤ የአላህ ባህሪዎች ከይፊያ የላቸውም ለማለት አይደለም። የሰው ልጅ ሊገነዘበውና ሊደርስበት የሚችል ከይፊያ ግን የለም፤ ማለታቸው ነው። የአላህን ባህሪዎች ምንነት “ከይፊያ” የሚያውቀው ግን አላህ እራሱ ብቻ ነው።

“ተምሢል” (ለአላህ ባህሪዎች አምሳያን ማድረግ)፦

 የአላህን ባህሪዎች ከፍጡራን ባህሪዎች ጋር ማመሳሰል ማለት ነው፡፡ አቻ እና ቢጤ ማድረግ ማመሳሰል ነው። ሙመሲላዎች “የአላህ መስሚያ እንደኛ መስሚያ ነው” ማለታቸው ምሳሌ ነው፤ አላህ ከእንዲህ አይነት ንግግሮቻቸው የላቀና የጠራ ነው።

 በቋንቋ ደረጃ ጥቂት ልዩነት ቢኖራቸውም “ተምሲል” እና “ተሽቢህ” አንድ አይነት ትርጓሜ ነው ያላቸው። ይሁንና በቁርዓን ላይ ከሰፈረው ቃል ጋር ስለሚሄድ “ተምሲል” የሚለውን ቃል በመጠቀም ውድቅ ማድረግ የተሻለ ይሆናል።

በ ”ተክዪፍ” እና በ”ተምሢል” መካከል ያለው መመሳሰልና ልዩነት፡-

 ከላይ እንደተገለጸው ተክዪፍ ያለማመሳሰል ሊፈጸም ይችላል። ማመሳሰል “ተምሲል” ግን የባህሪዉን ምንነት ከመገመት “ተክዪፍ” በኋላ የሚመጣ ነው። ስለዚህ፤ ተምሲል ሁሉ ተክዪፍ ነው። ትክዪፍ ሁሉ ግን ተምሲል አይደለም።

ብዙ የቢድዓ አራማጅ ቡድኖች ተክዪፍና ተምሲልን ይተገብራሉ። በዚህም ምክኒያት የኢስላም ሊቃዉንት “ሙሸቢሀ” ወይም “ሙመሲላ” በሚል ስያሜ ስር ይጠቀልሏቸዋል።

በዚህ ስር ከሚጠቃለሉት መካከል፤

1.ከራሚያህ- የሙሀመድ ቢን ከራም አሰጅስታኒ ተከታዮች ሲሆኑ አስራ ሁለት የሚሆኑ የተለያዩ አንጃዎች ናቸው።

2.ሂሻሚያህ- የሂሻም ኢብኑልሀከም ትከታዮች ናቸው። የሂሻም ቢን ሳሊም አልጀዋሊቂይ ተከታዮች እንደሆኑም ይታወቃል። ይሁንና እነዚህ ሁለቱም የራፊዳ (ሺዓ.. ኢስና ዓሸሪያህ) ተከታዮች ናቸው። ቀደምት ሺዓዎች የአላህን ባህሪዎች ከፍጡራን ባህሪዎች ጋር የሚያመሳስሉ ሙመሲላዎች ነበሩ። አሁን ያሉት ግን ሙዓጢላዎች ናቸው።

============= የአላህን ባህሪያት ስናጸድቅ ማወቅ የሚገባን ወሳኝ ገደቦች  ================

 የአላህ ስሞችና ባህሪዎችን ለማፅደቅ ትክክለኛው መንገድ አላህና መልዕክተኛው ያረጋገጡትን ያለ:-

  • “ተህሪፍ” (ትርጉሙ ሳይዛባ) ፣
  • ያለ “ተዕጢል” (ትርጉም የለሽ ሳይደረግ)፣
  • ያለ “ተክይፍ” (አይነቱ ሳይጠቀስ) እና ያለ
  • “ተምሢል” (አምሳል ሳይደረግለት) ማመን ነው፡፡

ተህሪፍ (ትርጉሙን ማዛባት)

   ተህሪፍ (ትርጉሙን ማዛባት) የተፈለገውን ትርጉም መቀየር ማለት ሲሆን በሁለት አይነቶች ይከፈላል፦

  1. “ተህሪፉ ለፍዝ” (ቃሉን ማጥመም) ይህ የሚሆነው የቁርአን ወይም የሀዲስ ቃላቶች ላይ ሌላ ቃልን በመጨመር፣በመቀነስ ወይም አነባቡን በመለወጥ ነው፡፡ለምሳሌ :-

ﺍﻟﺮَّﺣْﻤَٰﻦُ ﻋَﻠَﻰ ﺍﻟْﻌَﺮْﺵِ ﺍﺳْﺘَﻮَﻯ:طه :ه

 `ኢስተዋ` የሚለውን `ኢስተውላ` በሚል መቀየር:: (በዚህ… ሳቢያ አላህከ ዐርሽ ላይ በላይ ሆነ በሚል የሚሰጠውን ትርጉም ዐርሽን ተቆጣጠረ በሚል እንዲለወጥ ያደርጋል::)

  1. ተህሪፉል መዕና (ትርጉሙን ማጣመም) የቁርአንና የሀዲስን ቃሎች አላህ ባልፈለገው ትርጉም መተርጐም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ “የድ” (እጅ) የሚለውን ሀይል ወይም ፀጋ በማለት ትርጉሙን መለወጥ:: እንዲህ አይነቱ ትርጓሜ ሸሪዓውም ሆነ ቋንቋው አይቀበሉትም፡፡

ተዕጢል” (ትርጉም የለሽ ማድረግ)

  “ተዕጢል” (ትርጉም የለሽ ማድረግ) አላህ በምንም ባህሪ አይገለፅም ብሎ ማስተባበል ማለት ነው፡፡

በ”ተህሪፍ” እና በ”ተዕጢል” መካከል ያለው ለውጥ፡- “ተህሪፍ” ማስረጃዎች የሚደግፉትን ትክክለኛ ትርጉም በሐሰት ትርጉም መቀየር ሲሆን “ተዕጢል” ደግሞ ትክክለኛውን ትርጉም አግልሎ ያለ ተለዋጭ ትርጉም መተው ነው፡፡

ተክይፍየባህሪውን ሁኔታና አይነት መወሰን

 “ተክይፍ” የባህሪውን ሁኔታና አይነት መወሰን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የአላሀ እጅ እንዲህ አይነት ነው፣ አላህ ዐርሽ ላይ ሲደላደል በእንዲህ አይነት ሁኔታ ነው በመሳሰሉት መልኩ መዘርዘር ማለት ሲሆን ይህ ተግባር ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ከአላህ በቀር የእርሱን ባህሪ ሁኔታ የሚያውቅ የለም፤ ፍጡራን ይህን ማወቅ አይችሉም፡፡

ተምሢልየአላህን ባህሪያቶች ማመሳሰል

 “ተምሢል” የአላህን ባህሪያቶች ማመሳሰል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የአላህ መስሚያ እንደኛ ነው፣ የእርሱ ፊት እንደኛ ፊት ነው ማለት ነው፡፡

 በዚህ ርዕስ ውስጥ ሶስት መሰረቶችን ተግባራዊ ማድረግ በአላህ ስሞችና ባህሪዎች ዙሪያ የተስተካከለ አቋም እንዲኖር ይረዳል፡:

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here